Search

ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጋምቤላ ተካሄደ

ማክሰኞ መስከረም 20, 2018 162

የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በጋምቤላ ክልል፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የተገኙት የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን፥ በኢትዮጵያ ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ተቀብላ ያስጠለለቻቸው ስደተኞች ማንነታቸውን በግልፅ በመለየት የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችሉ ዘንድ አካታች የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ወይዘሮ ጠይባ ተናግረዋል።

ስደተኞችን እና ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦችን በልማት ለማስተሳሰርም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስታወቁት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ጥላሁን፥ በሀገሪቱ እስካሁን ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተመዝግበው የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት ደግሞ 40 ማሊዮን ያህል ዜጎችን በመመዝገብ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ሄኖክ አክለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ላክዲየር ላክባክ፥ በክልሉ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል የተጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በሀገሪቱ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋቱ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ስታቲስቲክስ እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፤ እውነተኛ ማንነትን በአግባቡ በመለየት  ወንጀልን ለመከላከል ጉልህ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክትም ተገልጿል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር

#EBCdotstream #Ethiopia #Gambella #NationalID #Refugees #HostCommunities