የ2ኛው የተባበሩት መንግስታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ አንዱ ትኩረት፤ ከፈረንጆቹ 2021 የምግብ ስርዓት ጉባኤ በኋላ በምግብ ሥርአቶች ለውጥ ላይ የተገኘውን እድገት መገምገም ነው።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጣሊያን ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ፣ የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሃመድ፣ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ኩ ዶንግዩ፣ የዓለምአቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ፕሬዝዳንት አልቫሮ ላሪዮ፣ የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የዩኤንዲፒ የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሃሙድ፣ የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶን ጨምሮ በርካታ ሚኒስትሮች እና ባልድርሻ አካላት ይሳተፋሉ።
በጉባኤው የሚጠበቁት አጀንዳዎች የሚያተኩሩት በዓለም የምግብ ሥርዓት ላይ በተገኙ ለውጦች፤ እንዲሁም ዘርፉን እየፈተኑ በሚገኙ ተግዳሮቶች ላይ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ከእነዚህም መካከል በዘርፉ እየተደረጉ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶች መስፋፋት፣ የምግብ ዋስትናን መገንባት፣ የትምህርት ቤት ምገባን ማስፋፋት እና ማጠናከር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ማሻሻያ እርምጃዎች እና ዘርፉን የሚያግዙ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ዋና ዋና የውይይት ማጠንጠኛዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በምግብ ስርዓት ዘርፍ ያላቸውን ልምድ፣ መምጣት ያለባቸውን ለውጦች እና እየታዩ የሚገኙ ለውጦችን ለማስቀጠል የሚረዱ እርምጃዎችን የያዙ ቁልፍ መልዕክቶችን በጉባኤው ያቀርባሉም ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ዋናው ግቡ የምግብ ሥርአቶች ለውጥን በማረጋገጥ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት በመሆኑ፤ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እና ትብብርን በሁሉም ዘርፎች ለማጎልበት ያግዛል ተብሎም ይጠበቃል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች፣ የሁለትዮሽ ውይይቶች እና ጉብኝቶች ይደረጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ጉባኤውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከጣሊያን ቴሌቪዥን እና ራዲዮ (Rai) ጋር በመተባበር በተለያዩ አማራጮች ለአድማጭ ተመልካቾች ያደርሳል።
በሰለሞን ከበደ