የፓን አፍሪካኒዝም መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን በራሳቸው ሀብታቸውን በመጠቀም መልማት አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ የቀየረ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተሰፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ቀንሳ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ እና ለኬንያ መሸጥ መጀመሯን በመጥቀስ ግድቡ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያንን ጭምር በልማት እያስተሳሰረ መሆኑንም ነው ዶ/ር ተስፋዬ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት።
በኢትዮጵያውያን ጥሪት፣ ላብ፣ ደም እና የሕይወት መስዋዕትነት የተገነባው ግድቡ ፋይዳው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሀገራት የሚተርፍ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑን አክለዋል።

ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ የራሷን ነፃነት አስጠብቃ ከመዝለቅ ባሻገር ለሌሎች ሀገራት የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል እና ነፃነት ታሪካዊ አበርክቶ ማድረጓን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ትውልድ የልማት አርበኝነት እውን የሆነ ዳግማዊ ዓድዋ እና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በርካታ ከባባድ ፈተናዎችን አልፈን የግዙፉን ግድብ ግንባታ ማጠናቀቃችን የመቻላችን ምልክት እንዲሁም የሞራላችን ከፍታ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBCdotstream #ETV #Ethiopia #Africa #GERD #gamechanger