Search

ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪ ተዋናይነቷን ያጠናከረችበት የሕዳሴ ግድብ

ረቡዕ መስከረም 21, 2018 52

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካውያን በቁርጠኝነት እና በአንድነት መቆም ከቻሉ፣ ያሰቡትን ማሳካት እንደማያቅታቸው ያሳየ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የዲፌንድ ኢትዮጵያ አውሮፓ የቤልጂየም አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ዘውዱ ተናገሩ።
የግድቡን ፕሮጀክት ከዳር ለማድረስ የተጓዝንበት መንገድ አልጋ በአልጋ አልነበረም ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ የሚዲያ ዘመቻና የሀሰት ትርክቶችን በመስበር በብዙ መሰናክሎች ውስጥ አልፎ የተሳካ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
አንዳንድ ሀገሮች ስለ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ በነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ 'የሕዳሴ ግድብ አይሳካም' የሚል አመለካከት እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን የተሳሳተ አመለካከት መስበር ችለዋል ነው ያሉት።
ከአባቶቻችን ገድል፣ ትጋትን እና ፅናትን በመማር ዛሬ ላይ ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማሳካት ችለናል ብለዋል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ የሀገር ገፅታን በመቀየር የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነትን እንደሚያጠናክረው ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ከግድቡ የምታመነጨው ታዳሽ ኃይል ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ በማድረግ፣ አዲስ የሀገራት የትብብር ምዕራፍን በመክፈት ቀጠናዊ ትስስርን ያጠናክራል ነው ያሉት።
በዚህም ሀገራት ከኢትዮጵያ በሚገዙት ታዳሽ ኃይል ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የስራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ