Search

በአረርቲ ከተማ ለሕንፃ ግንባታ የተረበረበ እንጨት በመደርመሱ እስካሁን ከ30 ሰዎች በላይ ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ

ረቡዕ መስከረም 21, 2018 191

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ ከተማ አስተዳደር አረርቲ ማርያም ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ክብረ በዓል እየተከበረ ነበር።
በዓሉን አስመልክቶም ከጠዋቱ 1:45 ላይ እየተሰራ ያለው ቤተክርስቲያን እየተጎበኘ ባለበት ‎ሰዓት ለፊኒሺንግ ሥራ የተረበረበው እንጨት ተደርምሶ በርካታ ምዕመናን ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል።
የአረርቲ ከተማ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ ለኢቢሲ እንደገለፁት፤ በአካባቢው በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የድንግል ማሪያም በዓልን አስመልክቶ በርካታ ምዕመናን በአካባቢው ይመጣሉ።
ዛሬ ከማለዳው 2:00 ላይ በቤተክርስቲያኑ ግንባታ የሕንፃ መወጣጫ የእንጨት ርብራብ መናድ አደጋ በርካቶች መጎዳታቸውን አንስትዋል።
የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ እና ከእንጨት ርብራቡ ሥር ያልወጡ ሠዎች በመኖራቸው የጉዳት መጠኑን መገመት አስቸጋሪ ነው ያሉት ኃላፊው፤ እስከአሁን የ30 ሠዎች ሕይወታቸው ማለፉ በሆስፒታል ተረጋግጧል ሲሉ አስታውቀዋል።
በተጨማሪ 55 ሰዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል።
ለተጎጂዎች የመጀመሪያ ሕክምና በአንድ ሆስፒታል እና በ4 ጤና ጣቢያዎች እየተሠጠ ነው ብለዋል።
ተጎጂዎችን ለማትረፍ ኅብረተሠቡ ጥረት ማድረጉን ያነሱት ኃላፊው፤ ከርብራቡ ሥር ያልወጡትን ዜጎችም ሕይወት ለማትረፍ እና ሕክምና እንዲያገኙ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።
የአረርቲ ሆስፒታል ኃላፊ ተወካይ አቶ ስዩም አልታዬ ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ ወደ አረርቲ ሆስፒታል የመጡ ተጎጂዎችን ሕክምና እየሠጠን ነው ሲሉ ለኢቢሲ የተናገሩት፤ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ተጨማሪ ድጋፍ ከወረዳ ባለሙያዎች እና አምቡላንሶችን በማቀናጀት እየሠራን ነው ብለዋል።
ከፍተኛ ጉዳት የደረሠባቸው 5 ተጎጂዎች ለተጨማሪ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን አስታውቀዋል።
በራሔል ፍሬው