‘ብላክ አፍሪክ ዳያሪ’ የተሰኘው እና በጥቁር አፍሪካውያን ታሪክ፣ ኪነ-ጥበብ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በማተኮር መረጃ የሚሰጠው የዩቲዩብ ቻናል፣ ስለ ሕዳሴ ግድብ ታላቅነት የዘረዘረበትን ዜና በሚቀጥሉት ጥያቄዎች ይጀምራል፦
“አንድ ፕሮጀክት ብቻውን ከዚህ ቀደም የኃይል አቅርቦት ላልነበረው ከግማሽ በላይ ለሚሆን የአንድ ሀገር ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይችላልን?
ለሺህ ዓመታት ሥልጣኔን በቀረፀ ወንዝ ላይ የተገነባ አንድ ፕሮጀክትስ ብቻውን የአፍሪካን የፖለቲካ ካርታ መቀየር ይቻላልን?
ጥያቄው በቅርቡ ስለተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሆነ መልሱ “አዎ ነው” ሲል ይመልሳል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በይፋ መርቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግድቡ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ይህ ታላቅ ግድብ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ታላቁ ስኬት ነው” ሲሉ ገልጸውት ነበር።
ይህ በ5 ቢሊዮን ዶላር የተገነባው ሜጋ ፕሮጀክት የተርባይኖች ድርድር እና የኮንክሪት ክምር ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ታሪክን ዳግም የመጻፍ፣ ሉዓላዊነትን ዳግም የመቀዳጀት እና የአፍሪካን የሕይወት መስመር ከመቶ ዓመታት በላይ የተቆጣጠረውን የኃይል መዋቅር ለመገዳደር የተደረገ ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ነው ሲል ይገልጸዋል ‘ብላክ አፍሪክ ዳያሪ’ በዘገባው።
ለኢትዮጵያ፣ ግድቡ በዓለም የገንዘብ ድርጅ (IMF) ወይም በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ ሳይሆን በዜጎቿ እና በዳያስፖራዎቿ ላብ እና መሥዋዕትነት የተገነባ በመሆኑ በራስ የመተማመን ድል መሆኑንም ይጠቅሳል።
ለዓለም ደግሞ አፍሪካ መፃኢ ጊዜዋን ለመገንባት የሌሎችን ፈቃድ ሳትጠይቅ በራሷ መወሰን የመጀመሯ ነፀብራቅ በመሆኑ እንደ ርዕደ መሬት የሚቆጠር ነው ሲል ይገልጻል።
እናም አሁን የምንጋፈጠው ጥያቄ ይህ ፕሮጀክት በግድብነት ብቻ የሚገለጽ ነው? ወይስ አፍሪካ ኃይሏን እንዴት መጠቀም እንዳለባት የሚያሳየን ነፀብራቅ ነው? የሚለው ነው ይላል።
ኢትዮጵያ፣ በአብዛኛው የ20ኛው ክፍለ ዘመን በኃያልነት ሳይሆን በረሃብ ትጠቀስ ነበር የሚለው የ‘ብላክ አፍሪክ ዳያሪ’ ዘገባ፣ በ1980ዎቹ ሲዘዋወር የነበረው በረሃብ የተጎዱ ሕፃናት ምሥል ለኢትዮጵያ የነበረውን አመለካከት ከመቀየሩም በላይ አብዛኛው አፍሪካ ጥገኛ፣ አቅም አልባ እና የራሱን ዕጣ ፋንታ መወሰን የማይችል አድርጎ በሌሎች አዕምሮ ውስጥ የሣለ መሆኑን ያወሳል።
ያ ታሪክ ታዲያ አሁን ላይ በሚያስደንቅ ሁኔታ መቀየሩን እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገሪቱን ከዓለም የዳር ፖለቲካ ወደ የአፍሪካ ፖለቲካ የኃይል ማዕከልነት እንድትመጣ ማድረጉን ያነሣል።
ግድቡን ግዙፍነት በመዘርዘርም፣ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እጥረት የነበረባት ሀገር አሁን ከዚያ ችግር መውጣቷ አንድምታው የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ከማግኘትም በላይ ነው ይላል ዘገባው።
ፀሐይ በጠለቀች ቁጥር ጨለማ ይሆን የነበረው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናም አሁን በሕዳሴው ግድብ አማካኝነት ቀስ በቀስ የኃይል አቅርቦት የማግኘት ዕድል እንዳገኘ፤ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አጥተው የቆዩት ኢንዱስትሪዎች አሁን ትኩረታቸውን የበለጠ መስፋት ላይ ማድረጋቸውን እና አጎራባች ሀገራትም ኢትዮጵያ ከምታቀርበው አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋ ማድረጋቸውን ያትታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለየት የሚያደርገው ግዙፍነቱ ብቻ ሳይሆን የተገነባበት ሁኔታ እንደሆነም እንደሚከተለው ይገልጻል፤ “ይህ ግድብ እንደሌሎች የአፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በዓለም ባንክ፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅት ወይም በቻይና ብድር ላይ ጥገኛ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ መገንባቱ ነው”።
የምዕራባውያን አበዳሪዎች በአብዛኛው በግብጽ ግፊት ለግድቡ ድጋፋቸውን ሲነፍጉ፣ ኢትዮጵያ ወደ ውስጥ አቅሟ መመልከት ጀመረች፤ ለመንግሥት ሠራተኞች የቦንድ ሽያጭ ተከናወነ፤ አርሶ አደሮች ካላቸው ላይ ቀንሰው ለግድቡ ሰጡ፤ መምህራን ከደመወዛቸው ላይ ተቆራጭ አደረጉ፤ የታክሲ ሾፌሮችም ከኪሳቸው አዋጡ፤ ዳያስፖራው ለቤተሰቡ የሚልከውን ሬሚታንስ ለፕሮጀክቱ እንዲውል አደረገ፤ ኢትዮጵያውያን ተባበሩ።
ይህ ፕሮጀክት ከላይ በሚደረግ የፋይናንስ አቅርቦት የተከናወነ ሳይሆን በሕዝብ አቅም የተከናወነ መሠረታዊ የኢንዱስትሪ አብዮት ነው ልንለው እንችላለን፤ እናም ከታሰበውም በላይ ውጤታማ ሆኗል ሲል ዘገባው ይገልጻል።
ይህ ደገሞ ተምሳሌታዊነቱ ችላ የማይባል ነው። በአንድ ወቅት የጥገኝነት መገለጫ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከየትኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነት ውጭ ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚችል አቅም ያለው ፕሮጀክት ገንብታለች። አፍሪካውያን ያለ ልመና በራሳቸው አቅም መገንባት ይችላሉ የሚል ግልጽ መልዕክትም ለዓለም አስተላልፋለች።
ነገር ግን እንዲህ ያለው ወደ ፊት የመዝለል ሁናቴ ነባሩን ሚዛን ማነቃነቁ እና በቀጣናው ያለውን የውኃን የመቆጣጠር እና የባለቤትነት ጉዳይን መቀስቀሱ አይቀሬ ነው ይላል ‘ብላክ አፍሪክ ዳያሪ’ በዘገባው።
የዓባይ ወንዝ ከወንዝነትም ባለፈ የሕይወት መስመር ነው፤ በተለይም ግብጽ 90 በመቶውን የመጠጥ ውኃ የምታገኘው ከዓባይ ወንዝ ነው። ለግብጽ ይህንን መብት የሰጠው ሕግ ግን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምንም ድምፅ ባልሰጡበት የተጻፈ ነው።
ግብጽ የሌሎች አፍሪካውያን ሐሳብ ያልተካተቱባቸውን የ1929ኙን እና የ1959ኙን ስምምነቶችን እንደ አሳሪ ሕጎች በመጠቀም የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የውኃን ፍሰት ሊያፋልሱ ይችላሉ ያለቻቸውን ፕሮጀክቶች እንዳይገነቡ ስታደርግ ቆይታለች።
የዓባይ ወንዝ ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ግን የራሷን ውኃ መጠቀም እንደማትችል በግልጽ ተነግሯት ለዘመናት ተገልላ ቆይታለች የሚለው ዘገባው፣ ሁኔታውንም ሲገልጸው፣ “በጓሮህ ከቆፈርከው የውኃ ጉድጓድ ምን ያህል ውኃ መጠጣት እንዳለብህ ጎረቤትህ ሲወስንልህ እንደማለት ነው” ብሎታል።
ለዚህም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ታሪክን የመጋፈጥ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀሰው።
ኢትዮጵያ የገነባችው መሠረተ ልማትን ብቻ አይደለም፤ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የራሳቸውን አንጡራ ሀብት እንዳይጠቀሙ ሉዓላዊነታቸውን የገፈፈውን ቅኝ አገዛዝን ጭምር ነው ያፈራረሰችው።
ካይሮ አሁንም እንደምትለው ግን ፕሮጀክቱ የኅልውናዋ ስጋት ነው፤ ለኢትዮጵያ ግን የሕዳሴው ግድብ የሉዓላዊነቷ መገለጫ ነው።
የሚገርመው ታዲያ ይህ እሰጥ-አገባ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ብቻ ተገድቦ የቀረ አይደለም የሚለው ዘገባው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፋዊ የኃይል መዋቅሮች በአፍሪካ ልማት ውስጥ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆኑ የሚያሳዩ ግብረ መልሶችን ማስተናገዱን ያወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እ.አ.አ በ2020 ከሱዳን እና ከኢስራኤል መሪዎች ጋር ባደረጉት የስልክ ለውውጥ፣ “ምናልባት ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳውም ትችላለች” ሲሉ መናገራቸውን አስታውሶ፣ ይህ በኋይት ሐውስ የተሰማው ንግግራቸው በመላው ዓለም ያሉ ዲፕሎማቶችን እንዳስገረመ ጠቁሟል።
ትንሽ ቆይቶም ዋሽንግተን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን በሚሊዮን የሚቆጠር ድጋፍ ማቋረጧን ጠቁሞ እነዚህ ድርጊቶች የሁኔታዎችን ውብስብነት ከማሳየታቸውም በላይ ውስጣዊ እውነታውን አጋልጠዋል ይላል።
የምዕራባውያን ተቋማት ከአፍሪካ ጥገኝነት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የራሳቸውን ጥቅም ሲያጋብሱ መኖራቸውንም ዘገባው ያትታል።
ኢትዮጵያ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ድጋፍ ውጭ ዜጎቿን አስተባብሯ ይህንን የመሰለ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክት መገንባት ከቻለች ለአፍሪካውያን ሳይሆን ለሌሎች በተለይም ከአፍሪካ ጥገኝነት ተጠቃሚ ለሆኑት አካላት አደገኛ ምሳሌ ትሆናለች።
ናይጄሪያ የራሷን ነዳጅ ለማውጣት የሚያግዛት የኢንዱስትሪ ተቋም ፋይናንስ ከማድረግ ምን ሊያስቆማት ይችላል? ዓለም ላይ ካለው የኮባልት ማዕድን የግማሹ ባለቤት የሆነችው ዴሞክራቲት ሪፐብሊክ ኮንጎስ ጥሬ ማዕድኗን ወደ ውጭ ከምትልክ የራሷን ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከመገንባት ምን ያግዳታል? ሲል ይጠይቅና፣ ለዚህ ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከውኃም በላይ የሚሆነው በማለት ግድቡ ለአፍሪካውያን የራሳቸው አቅም መፈተሻ ምሳሌ ሆኖ መምጣቱን ይጠቁማል።
ግድቡ አፍሪካ ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ሲበይን ለቆየው የዕርዳታ እና የዕዳ ጥገኝነት ሞዴል መሠረታዊ ፈተና እንደሆነበትም ይጠቅሳል።
ኢትዮጵያ ይህንን ሞዴል በመቀየር እና በመሠረታዊ የገንዘብ ድጋፍ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በማረጋገጥ ግብጽን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገራትን በጥገኝነት ጠልፎ የያዘውን ሥርዓት አንኮታኩታለች ይላል።
እንደዚህ ዓይነት የታሪክ ምዕራፎችን ለመጻፍ ታዲያ ተቃውሞ የማይገጥምበት ጊዜ በእጅጉ አነስተኛ ነው ሲል ኢትዮጵያ የገጠሟትን እና የተሻገረቻቸውን ፈተናዎችን ይዘረዝራል።
እ.ኢ.አ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የተከናወነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ልዩነቶችን በግልጽ አሳየ። በዕለቱ የኬንያ፣ የሶማሊያ፣ የጂቡቲ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ለምረቃው ጉባ ላይ ተገኙ። ግብጽ እና ሱዳን ግን ካለመገኘታቸውም በላይ ተቃውሞአቸውን በይፋ አሰሙ።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፓን-አፍሪካኒዝም መገለጫ ነው” ሲሉ አወደሱ።
ለበርካቶች ግድቡ የኢትዮጵያ ዕድገት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የመቻል ማሳያ ነው።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች እና ሕዝቦች የሕዳሴ ግድብ የጥገኝነት ማብቂያ የምሥራች እና አፍሪካ ራሷን በፋይናንስ አቅም መደገፍ እንደምትችል ማረጋገጫ መሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግድቡ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ጅማሮ እንጂ ፍፃሜ እንዳልሆነ፣ የኢትዮጵያ የልመና ዘመን ማብቃቱን እና አዳዲስ ሀገራዊ ራዕይዎችን ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በዜጎቿ አቅም ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ከገነባች፣ ነገ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች በፋይናንስ ለመደገፍ ምን ያግዳቸዋል? 360 ሚሊዮን አፍሪካውያን ዳያስፖራዎቸ በግድቦች፣ በኤርፖርቶች እና በኢንዱስትሪዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቢወስኑ ምን ሊከሰት ይችላል?
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ውኃ በዚህ መጠን የኃይል ሚዛንን መቀየር ከቻለ አፍሪካ አቅሟን በነዳጅ፣ በጋዝ ወይም በኮባልት ሀብቷ ላይ ብታውል ምን ሊፈጠር ይችላል? ሲል ይጠይቃል ዘገባው። መልሱም፣ "አዎ አፍሪካ ትችላለች" ነው።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #GERD #Africa #self_resilience #BlackArikDiary