የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር የጀመረው ስራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሠ ጫፎ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ባለፉት ዓመታት በምክክር ሂደቱ የተከናወኑ አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ተግባራት አፈፃጸም ሪፖርትን አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ሀገራዊ የምክክር ሂደት የዝግጅት ምዕራፍ ክንውኖችን፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተሳታፊ ልየታ ተግባራትን ዳሰዋል።
በዚህም በእስካሁኑ ሂደት በ11 ክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ተግባራት ማከናወን እንደተቻለ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር የገጽ ለገጽ እና የበይነመረብ (ቨርቿል) ውይይት መደረጉን አብራርተዋል።
በዚህም በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ በካናዳ ቶሮንቶ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ሌሎች ከተሞች አጀንዳ የማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ስኬታማ የምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በስዊዲን የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ምክክር እየተካሄደ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በቀጣይ ሳምንት ይኸው ስራ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልልም በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ ማካሄድ የሚያስችሉ ቅድመ ውይይቶች መካሄዳቸውን አብራርተዋል።
በዚህም በተለያዩ ጊዜያት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መካሄዳቸውን አንስተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን አለመግባባቶችን በምክክር መፍትሔ ለመስጠት ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት በተግባር ያረጋገጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን ለመፍጠር የጀመረው ሥራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን በኃላፊነት መንፈስ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ የሚያደርጉትን የነቃ ተሳትፎ በማጠናከር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስታላልፈዋል።
የሕዝብ ተካዮች ምክር ቤትም ለኮሚሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #NationalDialogue