Search

በመደመር መንግሥት መጽሐፍ በተመላከቱ ችግሮች ላይ መሥራት ወደምንፈልገው ከፍታ ይወስደናል፡- ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)

ሓሙስ መስከረም 22, 2018 42

ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)፥ በመደመር መንግሥት መጽሐፍ የተጠቀሱ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት፣ የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተፃፈው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ የተመላከቱ ችግሮች ላይ አተኩሮ መሥራት ወደምንፈልገው ከፍታ ይወስደናል ነው ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ።

ይህን ለማድረግ እንደ ደቡብ ኮሪያ እና ቻይና ያሉ ሀገራት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያመጡትን የኢኮኖሚ ለውጥ በመመልከት እኛም ከሠራን መለወጥ እንደምንችል ማሰብን ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የተለየ እምቅ የወጣት አቅም፣ የውሃ ሀብት፣ የእርሻ መሬት እና የማዕድን ባለቤት ናት፤ ሆኖም እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ልንጠቀምባቸው አልቻልንም ነው ያሉት።

ለዚህም ምክንያቱ አፍሪካውያን እንዳደጉ ሀገራት ከቅኝ ግዛት የእርሻ ኢኮኖሚ ወጥተን ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ከመሸጋገር ይልቅ ወደ አገልግሎት ኢኮኖሚ በመግባታችን ነው ብለዋል።

በዚህም የሚያስፈልገንን በሀገር ውስጥ ከማምረት ይልቅ ከውጭ አምጥተን መጠቀማችን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገን መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር በህዝብ ተሳትፎ እና ባህል ላይ የተመሠረቱ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ይመክራል ብለዋል።

የልማት ተዋናይ ህዝብ እንደመሆኑ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ አሳታፊ በሆነ መንገድ ህዝብን አደራጅቶ ወደልማት በማምጣት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል መጽሐፉን ዋቤ አድርገው አብራርተዋል።

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሀገራዊ ህልም ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራት የሚተርፍ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በቢታንያ ሲሳይ

#EBCdotstream #Ethiopia #YemedemerMengist