በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኘው ሶማሊ ክልል በነፋሻማ የአየር ንብረት፤ በሰፊ፣ ለም እና ሜዳማ መልክዓ ምድሩ እንዲሁም በእንስሳት ሀብቱ የሚታወቅ ክልል ነው።
ከዋና ዋና የተፈጥሮ ገጽታዎቹ መካከል “የያንጉዲ ራሳ” ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝ ሲሆን፣ የክልሉ ሕዝብ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ግብርና እና የእንስሳት እርባታ ነው።
ከባሌ ተራሮች የሚነሳው የሸበሌ ወንዝ ክልሉን አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚፈስስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ባይተዋር ሆኖ መሰደዱ በቅቶት የክልሉን ሰፊ መሬት ማልማት ጀምሯል።
ክልሉ ለረጅም ጊዜ በቂ ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ የመሠረተ ልማት እጥረት የነበረበት ቢሆንም፣ ወደ ሰላም እና ልማት በተመለሰባቸው ያለፉት ሰባት ዓመታት ግን አዳዲስ መንገዶች እና የመገናኛ አውታሮችን ለማሻሻል በተሠሩት ሥራዎች ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።
የሶማሊ ክልል ሕዝብ የኢትዮጵያን ወሰን አስከብሮ ለዘመናት የዘለቀ የኢትዮጵያ ጠንካራ አጥር ነው። ክልሉ በምድሩ ያቀፈው ከፍተኛ ሀብትም በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች ለክልሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል።
በ2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ መንግሥት ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሰረት በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ONLF) የሰላም ስምምነቱን አክብሮ ወደ ሰላማዊ ትግል በመግባቱ ክልሉ ወደ አስተማማኝ ሰላም ተመልሷል።
በዚህም ምክንያት በአንድ ወቅት በጦርነት፣ በድርቅ እና በመጠረተ ልማት እጦት ረገድ ባጋጠሙት ፈተናዎች ይታወቅ የነበረው ክልሉ በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሞተር ለመሆን በመንደርደር ላይ ይገኛል።
ሰፊውን እና ለሙን የክልሉን መሬት በሜካናይዜሽን ለማልማት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ ይህም ክልሉ በሰብል ምርት ራሱን ከመቻል አልፎ ኢትዮጵያን እንዲመግብ የሚያስችለው የተስፋ ስንቅ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህም የሶማሊ ክልል በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ እንዲሆን በማድረግ እንደ ዳንጎቴ ግሩፕ ያሉ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ አስችሎታል።
ታላላቅ ፕሮጀክቶች የክልሉ ዋነኛ ትኩረት ከመሆናቸውም በላይ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት ከነበረው አሳሳቢ የፀጥታ ችግር ወጥቶ ወደ ሰላም እና መረጋጋት የመጣበት ፈጣን ለውጥ ለሌሎች ክልሎችም አርዓያ የሚሆን ነው።
በክልሉ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ካሉብ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ዙር ተጠናቅቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምርቃቱ የተበሰረ ሲሆን፣ ይህም ለኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን ብሥራቶች አንዱ ሆኗል።
የተስፋዋ ምድር ጎዴ
ጎዴ በሶማሊ ክልል ከሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች አንዷ ስትሆን የሸበሌ ዞን አስተዳደራዊ ማዕከል ነች። ከተማዋ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ የሶማሊ ክልል መንግሥት መቀመጫም ነበረች።
ከክልሉ ዋና ከተማ ጂግጂጋ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ጠረፍ አካባቢ የምትገኘዋ ጎዴ ከአዲስ አበባ 638 ኪ.ሜ ገደማ ላይ ትገኛለች። በየብስም በአየርም ቀጥታ ወደ ከተማዋ የሚያደርስ መሰረተ ልማት የተሟላላትም ነች ጎዴ።
የኡጋስ ሚራድ አውሮፕላን ማረፊያ የ"IATA code GDE" ኮድ የተሰጠው ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዕለቱ ቋሚ በረራ ወደዚያው ያደርጋል።
ለም በሆነው የሸበሌ ወንዝ ዳርቻ ላይ የምትገኘው ይቺ ከተማ አካባቢዋን ለም ለም የእርሻ መሬት በማድረግ የኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫትነት እውን ለማድረግ የሚያስችል ተፈጥሮ የተከበበች የምድር ገነት ነች።
የሸበሌ ወንዝ ለም እና ሰፊውን የጎዴ መሬት በማረስረስ አካባቢውን ወሳኝ የምጣኔ ሀብት ማዕከል የሚያደርግ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።
ጎዴ ባለፉት ሰባት ዓመታት እያሳየችው ባለው የልማት እና የሰላም እንቅስቃሴ እጅግ አስደናቂ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
ከድንበር ጠባቂነት ወደ ኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ማዕከልነት እየተሸጋገረችም ነው። ተፈጥሮ ባደላት ስጦታዋ የብዙዎች ተስፋ የነበረችው ጎዴ አሁን ያ ተስፋ እንጀራ የሚሆንበት ጊዜ ላይ ደርሷል።
በሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በሀገሪቱ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ሽግግር የአንበሳውን ድርሻ ለመጫወት እየተጋች ትገኛለች።
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ እጅግ እየተሻሻለ ያለ የመንገድ መረብ እንዲሁም የተሻለ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት ባለቤትም ሆናለች።
እነዚህ ማሻሻያዎች ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ከማድረጋቸውም ባለፈ የነዋሪዎቿን አጠቃላይ የኑሮ ጥራት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው።
ቀደም ሲል ጠፍ የነበረውን መሬት እንደ ስንዴ፣ በቆሎ እና ሌሎች ሰብሎች በመሸፈን ወደ ምርታማነት ገብታለች። በዚህም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ጉዞም በመደገፍ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር የራሷን ድርሻ እየተወጣች ትገኛለች።
የትዮጵያ አርሶ አደሮች ተስፋ፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ የሆነው እና ዳግማዊ ሕዳሴ የተባለው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ አማካኝነት በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ሊገነባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማዳበሪያ ፋብሪካውን መሰረት ሲያስቀምጡ፣ "የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ ጋዝ በማውጣት እና 108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ ያቀርባል" ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት ለሶማሊ ክልል እና ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን ነጻነት ምሉዕ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቁን አሻራ የሚያሳርፍ ነው።
በየዓመቱ እስከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የሚያመርተው የማዳበሪያ ፋብሪካው ኢትዮጵያን ከዓለማችን ማዳበሪያ አምራቾች አንዷ ያደርጋታል።
ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ከውጭ በሚገባው የማዳበሪያ ምርት ላይ ያላትን ጥገኝነት በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን የሚቆጥብ ከመሆኑም በላይ ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።