ኢሬቻ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተዉ ድንቅ እሴቷ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የኢሬቻ በዓልን አስመልክቶ ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ኢሬቻ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተዉ ድንቅ እሴቷ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለዓለም አበርክታለች፡፡ እሴታቸዉን ጠብቀዉ ለዘመናት በሕዝብ እየተከበሩ የዘለቁ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትንና ትውፊቶቻቸዉን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት ተብለው እንዲመዘገቡም አድርጋለች፡፡ ለምዝገባ በሂደት ላይ የሚገኙ በርካታ እሴቶች ባለቤትም ነች፡፡
ኢሬቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር የይቅርታ እና የምስጋና በዓል ነው፡፡ በዓሉ በዋናነት ክረምት በሰላም አልፎ ዐዲስ ዘመን መበሰሩን አስመልክቶ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡
ምስጋናዉ ደግሞ ይቅርታን ያስቀድማል፤ የተጣላ ይቅር ተባብሎ በአንድ ቦታ ለፈጣሪዉ ምስጋና የሚያቀርብበት ነውና፡፡ ይህ ድንቅ የኢትዮጵያ እሴት የዓለም ሀብት እንዲኾን ኢትዮጵያ ለዘመናት ጠብቃዋለች፤ ትጠብቀዋለችም፡፡ የሚጠበቀዉ ደግሞ በዓሉን ትውፊቱን፣ እሴቱን፣ አሳታፊነቱን ጠብቆ በማክበር እና በማስተዋወቅ ነው፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እና መላዉ ኢትዮጵያውያን የዘንድሮዉን የኢሬቻ በዓል ምስጋና የሚያቀርቡት በጋራ ድላቸው ያሳኩትን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የደስታ ስሜት እያጣጣሙ ነው፡፡ በይቅርታ መሻገር፤ በጋራ ድል ማድረግ፤ በጋራ ማመስገን የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነውና፤ እንደ ኢሬቻ ያሉ የይቅርታ እና ምስጋና እሴቶች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት