Search

ሐሳብ አስማሚዋ፣ የአንድነት እና የመደመር መንፈስ ማሳያዋን ሲንቄ ማን እና እንዴት ይይዟታል?

ቅዳሜ መስከረም 24, 2018 822

በኦሮሞ ሕዝብ መተዳደሪያ ሥርዓት (ገዳ) ውስጥ ከተደነገጉ ድንጋጌዎች አንዱ ለሲንቄ የተሰጠ ሥልጣን አክብሮት (ሰፉ) አንዱ ነው።

ሲንቄ ከዝግባ ዛፍ የሚዘጋጅ፣ በሴቶች ብቻ እንዲያዝ የተፈቀደ ዘንግ ነው። ዘንጉ ከዘንግነት በዘለለ የሴቶች ሥልጣን መገለጫም ነው።

በመጀመሪያ ሲንቄ የሚሰጠው ከእናት ለሴት ልጅ ሲሆን፣ ሲንቄ ከልጃገረድነት ወደሴትነት የመሻገርዋ የክብር ምልክት እና ወግ ነው።

በመሆኑም በኦሮሞ ባህል መሠረት ማንኛዋም ያገባች ሴት ሲንቄ አላት። ነገር ግን ሲንቄ ያለሥርዓት (‘ሲርና’) ዝም ተብሎ ተይዞ አይወጣም።

ሲንቄ አግብታ ለወግ ለማዕረግ የደረሰች ሴት ብቻ የምትይዘው ሲሆን፤ አንዲት ሴት ሳታገባ አርጅታ ሽበት ብታወጣ እንኳ ሲንቄ መያዝ (ሐደ ሲንቄ መሆን) አትችልም።

ሲንቄ በበርካታ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ይያዛል። ከነዚህም መካከል ሃደ ሲንቄዎች ለዝናብ ልመና ወደ መልካ ሲወርዱ ወይም ወደ ኮረብታ ሲወጡ እና ሠርግ ተጠርተው ሲሄዱ ይይዙታል።

የሲንቄ ሥልጣን መገለጫነት ዘርፈ ብዙ ነው። አንዲት ሴት በተለይ በአራስነት ወይም በእርግዝና ጊዜዋ በባሏ ከተመታች እና የድረሱልኝ ጥሪ ካቀረበች ሰፈርተኛው ሴት በሙሉ ሲንቄ ይዞ ይወጣል። በዚህ ጊዜም የሐደ ሲንቄዎቹ ባሎች አትሂዱ ብለው ማስቆም አይችሉም።

ሐደ ሲንቄዎች ተሰብስበው አቴቴ ይላሉ፣ ባልየው ተቀጥቶ፣ ፊታቸው ወድቆ ይቅርታ ጠይቆ፣ ሚስቱን አልብሶ ጉዳዩ በእርቅ እስኪያልቅ የትኛዋም ሴት ወደቤት አትገባም።

ሰፈሩ ይጨነቃል፤ ከብት አይታለብም፤ ጥጆችም ይጮኻሉ። በዳይ የታወቁ የሀገር ሽማግሌዎችን ለምኖ በወግ በሥርዓት መሠረት ተለምነው ያቆማሉ።

በአንድ መንደር ግጭት ሲፈጠር ደግሞ ጉዳዩ ወደ ከፋ ነገር ከመሻገሩ በፊት ሐደ ሲንቄዎች ወጥተው ይለምናሉ። ይህ ደግሞ ሌላው የሲንቄ ሥልጣን መገለጫ ነው።

ፀበኞች አመፁን ለማቆም ፈቃደኛ ካልሆኑ ግን ሲንቄያቸውን በፀበኞቹ መካከል ያጋድማሉ። በዚህ ጊዜ ማንም ሰው፣ ሲንቄዎቹን ተራምዶ አይሔድም።

ሴቶች በየትኛውም ወቅት ሲንቄ ይዘው በቡድን ሲሔዱ ያየ ሰው ፈረሰኛም ቢሆን ከፈረሱ ወርዶ ቆሞ ጠብቆ፣ አጠገቡ ሲደርሱም እርጥብ ሣር ወደ እነርሱ እየበተነይቅር በሉኝ፣ አሳልፉኝብሎ ይጠይቃል።

ካለፉ በኋላም ያልፋል፣ ማንም ሰው አባገዳ እንኳ ቢሆን ሲንቄ የያዙ ሴቶችን መንገድ አያቋርጣቸውም። ይህም ለሴት ልጅ የሚሰጠውን ከፍተኛ ክብር ያመላክታል።

ሌሎች የሲንቄ ሥልጣን ማሳያዎችም አሉ። ቤት ውስጥም ቢሆን ባሎች ሚስቶቻቸውን የሚመቱበት ኋለቀር ልማድ ከሲንቄ ክብር ጋር የሚፃረር ነው።

ሚስቱ ሲንቄ የያዘች ባል ሲንቄዋን ከእጇ ተቀብሎ አይመታትም፣ አድርጎት ከተገኘም ለአባገዳዎች ተነግሮ ምክንያቱ እንኳ ሳይጠየቅ ይቀጣል።

በጥንቱ ባህል ሰውየው ራሱ አካላዊ ቅጣት ሊቀጣ ይችላል። በቅጣቱ ማቄም አይፈቀድም። በአጠቃላይ ሲንቄ የማጌጫ ዘንግ ብቻ ሳይሆን የሴት ልጅ መከበርያ እና ሥርዓት ማስከበርያ ዘንግ ነው።

ሲንቄ የተጣሉትን አስታራቂ፣ የተለያዩ ሐሳቦችን አስማሚ፣ የአንድነት እና የመደመር መንፈስ ማደሪያ፣ የሀገር ማፅኛ ዘንግ ነው።

በሴራን ታደሰ