Search

ኢትዮጵያ በሱዳን ለደረሰው ጎርፍ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ተደርጎ የቀረበውን ክስ ውድቅ አደረገች *****************************************

ቅዳሜ መስከረም 24, 2018 195

ኢትዮጵያ በሱዳን ለደረሰው ጎርፍ የሕዳሴ ግድብ ምክንያት ተደርጎ የቀረበውን ክስ ውድቅ አደርጋለች።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በዓባይ ወንዝ ላይ የግብፅ መንግስት ተቋማት የሚያወጡት መግለጫ በውሸት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሀገሪቱ እና ተቋሞቿ ለረጅም ጊዜ ሲያደርጉት እንደቆዩት፤ የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር በሐሰት እና ቅራኔ የተሞላ ብሎም የተዛባ መግለጫን ከሰሞኑ አውጥቷል።

መግለጫው ተንኮል-አዘል እና በርካታ መሠረተ ቢስ የይገባኛል ጥያቄዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ጉዳዩን በገለልተኛ አቋም ለሚመለከተው ሰው ይህ ግልጽ ጉዳይ እንደሆነም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫው ጠቁሟል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በፊት ያለውን የጥቁር ዓባይ ፍሰት ታሪካዊ መረጃ እና አሁን ያለውን የወንዙ የፍሰት መረጃ መመልከት እውነታው የት ላይ እንዳለ በግልፅ ያሳያልም ብሏል።

በሱዳን ለተከታታይ 93 ዓመታት የተመዘገበው የፍሰት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በነሀሴ ወር እና በመስከረም ወር ከፍተኛ ጎርፎች ይከሰቱ ነበር።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የጎርፍ መጠንን የቀነሰ እና ይደርስ የነበረውን ጉዳት በእጅጉ የቀነሰ መሆኑንም የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው ጠቁሟል።

የሕዳሴው ግድብ ባይኖር ኖሮ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ከፍተኛ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ፤ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን ላይ ከባድ ጎርፍ ያስከትል እንደነበርም ግልጽ ነበር ብሏል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ።

ዓመቱን ሙሉ የተስተካከለ ፍሰት እያገኙ ያሉት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠቃሚዎች ነው የሆኑትም ብሏል መግለጫው።

የግብፅ መግለጫ መሰረተ ቢስ እንደሆነም ጠቅሶ፤ የሱዳን የግብርናና መስኖ ሚኒስቴር መግለጫ እንደሚያመለክተው በሱዳን የሚታየው የጎርፍ አደጋ መንስኤ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የናይል ገባር ከሆነው ከነጭ አባይ የሚወጣው የውሃ ፍሰት መጨመር እንደሆነም በግልጽ ማስቀመጡን ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ኃላፊነት የሚሰማት ሀገር እንደመሆኗ ከጎረቤት ሱዳን ጋር የመረጃ ልውውጥ እና ትብብር ለማድረግ አስፈላጊውን ማዕቀፍ እንደዘረጋች የጠቆመው መግለጫው፤ ኢትዮጵያ በካርቱም ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ በመከላከል ሕዳሴ ግድብ ለሱዳን በረከት ሆኖ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው የሱዳን ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ መስራቷን ትቀጥላለችም ነው ያለው።

ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን በመገንባትና በመስራት ልምድ ያላት ሀገር ስትሆን፤ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ግድቦቿን በከፍተኛ የሙያ ብቃት የማስተዳደር አቅም እንዳላትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጽንኦት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ የግብፅን የሀሰት ውንጀላ እና የስም ማጥፋት መግለጫን ሙሉ በሙሉ እንደማትቀበልም ገልጾ፤ ግብፅ በናይል ተፋሰስ ውስጥ የበላይነት አለን የሚለውን የተሳሳተ ሀሳብ ትታ በጋር ለጋራ ብልፅግና ብንሰራ መልካም ነው ብሏል በመግለጫው።

የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ እና የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ኩራት ሆኖ ብሎም በመላ አፍሪካ እና በአፍሪካ ልማትን የሚደግፉ ሀገራት ተከብሮ ይቀጥላል።

የአፍሪካ የልማት ግዞ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ መገለጫ በሆነው "ታሪካዊ መብቶች" የሚል የሀሰት ትርክት የሚገታ አይሆንም፤ ግብፅ ያለፈውን ዘመን እሳቤ የምተውበት ጊዜ አሁን ነው ብሏል በመግለጫው።