Search

"ለጥርስ እና ለዐይን ሕክምና ውጭ ሀገር እንዳትሄዱ፤ የተሻለ እዚህ አለ!" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ጥር 27, 2018 77

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ በልዩ ሕክምና እና በመሠረተ ልማት ረገድ እያሳየ ያለው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ሥር ነቀል ሪፎርሞችን በቁጥር አስደግፈው አቅርበዋል።

በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 37 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማደጉን፤ ይህም ቀደም ሲል 100 ሺህ እናቶች መካከል 400 ገደማ ይሞቱ የነበረውን ቁጥር ወደ 141 ዝቅ እንዲል ማድረጉን አንሥተዋል።

የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ፍጆታ ምርት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት 8 በመቶ አሁን ላይ 42 በመቶ ደርሷል፤ ይህም ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።

ገና ብዙ ሥራ ቢጠብቀንም ከአምስት ዓመት በታች እና የጨቅላ ሕፃናት ሞት ምጣኔ መቀነሱንም ጠቁመዋል።

የማርበርግ ወረርሽኝን ቶሎ በማወቅ እና በማሳወቅ፣ ላብራቶሪ በማደራጀት እና ባለሙያ በማሰማራት በተሠራው ሥራ በሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሉ ትልቅ እርምጃ ነው።

መንግሥት ለካንሰር ሕክምና እስከ 60 በመቶ ድጎማ እንደሚያደርግ በማስታወስ፣ በሕክምናው ዘርፍ ሕዝቡን ለመደገፍ ሰፊ ድጎማ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድኃኒት ሥርጭት ላይ የሚታየውን ሌብነት እና የአቅርቦት ችግር ለመፍታትጤናዬየተሰኘ መተግበሪያ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ይህ "ኦቶሜሽን" ሥርዓት በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ግልጽነትን በመፍጠር ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመለየት የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

ጥቂት ቢሆኑም በሙያቸው የተመሰገኑ ኢትዮጵያውያን ልምዳቸውን እና እውቀታቸውን ይዘው መጥተው ሥራ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።

በተለይም የዐይን እና የጥርስ ሕክምናን በተመለከተ ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ከመታከም ይልቅ በሀገር ውስጥ ባሉ ምርጥ ባለሙያዎች እንዲታከሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከአሜሪካ መጥተው በኢትዮጵያ የዐይን እና የጥርስ ሕክምና ተደርጎላቸው የተመለሱ ቤተሰቦችን እንደ ምሳሌ አንስተዋል።

"እንዴት ሰው ከአሜሪካ መጥቶ ኢትዮጵያ ይታከማል?" የሚል ጥያቄ አድሮባቸው ጉዳዩን ማረጋገጣቸውን ገልጸው፣ "በተለይ ለጥርስ እና ለዐይን ሕክምና ውጭ ሀገር እንዳትሄዱ፤ የተሻለ እዚህ አለ!" ሲሉ በኢትዮጵያ በተፈጠረው ጠንካራ የሕክምና ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ዘመናዊ የሕክምና ማዕከላትን መክፈታቸው ለዚህ ውጤት መገኘት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከዚህ ቀደም "ጤና ከኩሽና ይጀምራል" በማለት የሥነ-ምግብ ጉዳይ ለጤና ያለውን ወሳኝነት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በዚህም ጤናማ እና አምራች ዜጋ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በሀገር ደረጃ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በሽታን ቀድሞ መከላከልን መርሕ ባደረገ ሥራም በከተሞች የሚገነቡ መናፈሻዎች እና ንጹህ አካባቢዎች ለአዕምሮ እና ለአካል ጤና ያላቸውን ፋይዳ በተግባር አሳይተዋል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #AbiyAhmedAli #health #tenayeapp