የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ሀገራት (በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ) አስተናጋጅነት ሊካሄድ ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተዋል። ውድድሩ በ48 ሀገራት ተሳትፎ ደምቆ እንደሚካሄድ ቢጠበቅም፣ አሁን ላይ ግን ከስፖርታዊ ጉዳዮቹ ይልቅ በፖለቲካዊ ውጥረቶች የታጀቡ የ"ቦይኮት" ወይም የማግለል ጭምጭምታዎች ዓለም አቀፉን ስፖርት እየተፈታተኑት ይገኛሉ።

በተለይም ከአውሮፓ ሀገራት የሚሰሙት የተቃውሞ ድምፆች ስፖርት እና ፖለቲካ ያላቸውን የማይነጣጠል ቁርኝት ዳግም ወደ አደባባይ አውጥተውታል። የአውሮፓ ሀገራት የሚያሰሙት የማግለል ጥያቄ ገና በጭምጭምታ ደረጃ ያለ ቢሆንም፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ መሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ ሲሄድ ውጥረቱ ወደ እውነተኛ "የእግር ኳስ ጦርነት" ሊቀየር እንደሚችል ስጋቶች አሉ። ይህም የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ በታሪክ ከፍተኛ ውዝግብ የሰፈነበት እና የስፖርቱ ውበት በፖለቲካ ጥላ የተሸፈነበት ሊያደርገው ይችላል።
የ2026 ዓለም ዋንጫ ስጋት መነሻዎች
በአሁኑ ወቅት በተለይም በጀርመን፣ በኔዘርላንድስ እና በስካንዲኔቪያ ሀገራት በደጋፊዎች እና በአንዳንድ የፖለቲካ ክበቦች ዘንድ የ2026ቱን ውድድር "የማግለል" ጥሪዎች እየተሰሙ ነው። የዶናልድ ትራምፕ መንግሥት በቬንዚዎላ መሪ ላይ የፈጠሩት አጀብ ያሰኘ ክስተት የፈጠረው የግርምት ስሜት ሳይጠፋ በግሪላንድ ላይ ያነሱት የይገባኛል ሀሳብ ዓለምን ወደ ሌላ አቅጣጫ የገፋ ሆኗል።
በተለይም የአውሮፓ ሀገራት በተለየ ሁኔታ ከአሜሪካ ጋር በተቃራኒ ለመቆም ያሰቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህ አበይት የሆነውን ምክንያት ሀገራቱ ራሳቸው ቢያውቁትም አሁን እያነሱት ላለው “ከ2026ቱ ዓለም ዋንጫ እናግል” ሀሳብ መነሻ ምክንያቶች የመጀመሪያ፣ የአሜሪካ መንግሥት በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች (የግሪንላንድ ጉዳይ እና በላቲን አሜሪካ ጣልቃ ገብነት) ላይ ያለው አቋም በአውሮፓውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል የሚል ነው። የህ ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ሀገራት ልዩነታቸውን ወደ ስፖርት በማምጣት የፍልሚያውን መድረክ ስፖርት ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው።
በተለይ በአሜሪካ ድንበሮች ላይ የሚስተዋለው የስደተኞች አያያዝ እና ተያያዥነት ያላቸው ጥብቅ የፖሊስ እርምጃዎች፣ እንደ ጀርመን ባሉ ሀገራት ለሚገኙ የስፖርት ማህበራት ዋነኛ የመከራከሪያ ነጥብ ሆነዋል። እነዚህ ማህበራት የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ የሰብአዊ መብት መከበሪያ መድረክ እንዲሆን በመጠየቅ፣ ዓለም በጉጉት የሚጠብቀውን ይህን ታላቅ ውድድር በአሜሪካ መንግሥት ላይ የዲፕሎማሲያዊ ጫና ማሳደሪያ ለማድረግ ያሰቡ ይመስላሉ።
ከዚህም ባለፈ ለአንዳንድ ሀገራት ዜጎች የሚጣለው የጉዞ ገደብ በተጫዋቾች፣ በልዑካን ቡድን አባላት እና በደጋፊዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሌላው የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ቀርቧል። ይህም ፊፋ ሁሉንም አባል ሀገራት ያለ አድልዎ የማስተናገድ መርሁን የሚጻረር በመሆኑ፣ ሀገራቱ በውድድሩ ላይ ባለመሳተፍ ጠንካራ ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ የሚገፋፋ ምክንያት ሆኗቸዋል። ይህ የቪዛ እና የጉዞ ዋስትና ጥያቄ፣ ስፖርቱ ከፖለቲካዊ ውሳኔዎች ነፃ መሆን እንዳለበት የሚገልጸውን ዓለም አቀፍ መርህ የሚፈትን አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
የታሪክ ትዝታዎች፦ ስፖርት የፖለቲካ ፍልሚያ መድረክ ሲሆን
በስፖርቱ ታሪክ ውስጥ ሀገራት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ላለመሳተፍ የሚወስኑት የማግለል እርምጃ አዲስ ክስተት አይደለም። ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች በከረረ የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ በገባች ቁጥር፣ የጦርነቱ አንደኛው አውድማ የስፖርት መድረክ ሲሆን በተደጋጋሚ ተስተውሏል። ከዚህ ቀደም የታዩ ማግለሎች ዝም ብለው የታዩ ተራ ክስተቶች አልነበሩም፤ ይልቁንም በአትሌቶች ሕይወት፣ በሀገራት ዝና እና በውድድሮች ጥራት ላይ የማይፋቅ ጠባሳ ጥለው ያለፉ የታሪክ ክስተቶች ናቸው።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው እና በተደራጀ መልኩ የተመዘገበው ስፖርታዊ ማግለል የተከሰተው በ1956ቱ የሜልበርን ኦሎምፒክ ላይ ነበር። ምንም እንኳን ከዚያ ቀደም ብሎ በ1936ቱ የበርሊን ኦሎምፒክ ወቅት የአይሁድ አትሌቶች የግል ማግለል ታይቶ የነበረ ቢሆንም፣ በሀገር ደረጃ ውድድሩን አንሳተፍም ብለው በይፋ የወጡት ግን በዚህኛው የ1956ቱ ክስተት ነው። የሚገርመው ግን ይህ የመጀመሪያው ማግለል የተከሰተው በአንድ ምክንያት ሳይሆን በሦስት የተለያዩ ፖለቲካዊ ግጭቶች ሳቢያ ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ተከፋፍላ በነበረችበት ወቅት መሆኑ ነው።
በወቅቱ የታዩት ግጭቶች የዓለምን ስፖርት ለሦስት የከፈሉ ነበሩ
አንደኛው የእስራኤል፣ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ጦር የሱዌዝ ቦይን ለመቆጣጠር በግብፅ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት በመቃወም ግብፅ፣ ኢራቅ እና ሊባኖስ ራሳቸውን ከውድድሩ ሲያግሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሶቪየት ህብረት በሀንጋሪ ላይ ያደረገችውን ወታደራዊ ወረራ በመቃወም ኔዘርላንድስ፣ ስፔን እና ስዊዘርላንድ ራሳቸውን አግልለዋል።
በተጨማሪም የኦሎምፒክ ኮሚቴ ታይዋንን በገለልተኛ ሀገርነት እንድትሳተፍ በመፍቀዱ የተቆጣችው ቻይና፣ ይህንን "ሁለት ቻይናዎችን የመፍጠር ሴራ" በማለት በመቃወም በሜልቦርን ኦሊምፒክ ሳትሳተፍ ቀርታለች። ይህ ክስተት ስፖርት እንዴት የፖለቲካ የበቀል መወጫ መድረክ ሊሆን እንደሚችል የመጀመሪያውን ታሪካዊ አሻራ ጥሎ አልፏል።
ኦሊምፒክና የፖለቲካ ቁርሾዎች፦ ከሞንትሪያል እስከ ሞስኮ
በስፖርት ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ጠባሳ ጥለው ካለፉ ክስተቶች መካከል የ1976ቱ የሞንትሪያል ኦሊምፒክ አንዱ ነው። ይህ ማግለል የተካሄደው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ22 የአፍሪካ አገራት መሪነት ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ የኒውዚላንድ የራግቢ ቡድን በአፓርታይድ ትተዳደር ወደነበረችው ደቡብ አፍሪካ ሄዶ መጫወቱን በመቃወም ነበር። በርግጥ ይህ እርምጃ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መድረክ ድምፃቸውን እንዲያሰሙና ዘረኝነትን እንዲያጋልጡ ረድቷቸዋል በሚል እንደ በጎ ተፅዕኖ ቢነሳም፣ በሌላ በኩል ግን እንደ ኢትዮጵያውያኑ ምሩፅ ይፍጠር፣ ሻምበል መሀመድ ከድር እና ሻምበል እሸቱ ቱራ ያሉ ድንቅ አትሌቶች በብቃታቸው ማማ ላይ ሳሉ በፖለቲካ ምክንያት ሳይወዳደሩ እንዲቀሩ አድርጓል።
ምሩፅ ይፍጠር በ1972 አሸንፎ በ1976 ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ እንደሚቀዳጅ ቢጠበቅም ሳይሳተፍ ቀርቷል። ለዚህም ነው ከዓመታት በኋላ በ1980 ሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ "ተስፋ የቆረጠው አትሌት" ተብሎ ወርቅ ያገኘው። ከዚህ በተጨማሪ የረጅም ርቀት ውድድሮች የአፍሪካውያን የበላይነት የሚታይባቸው በመሆኑ፣ የእነሱ በሞንትሪያል አለመኖር ውድድሩን ጥራት የጎደለው አስኝቶታል።
ከአራት ዓመታት በኋላ የተካሄደው የ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክም በተመሳሳይ የፖለቲካ ማዕበል ተመትቷል። ሶቪየት ህብረት አፍጋኒስታንን መውረሯን በመቃወም አሜሪካ የመራችው ሰፊ የማግለል ዘመቻ ከ60 በላይ ሀገራት እንዳይሳተፉ አድርጓል። ይህ ድርጊት በአሜሪካ እና በሶቪየት ህብረት መካከል የነበረውን "የቀዝቃዛ ጦርነት" ይበልጥ እንዲፋፋም አደረገው እንጂ ሰላምን አላመጣም። ለውድድሩ ለአራት ዓመታት ሌት ተቀን የለፉ አትሌቶች ህልማቸው በአንድ ጀምበር ሲከሽፍ፣ ብዙዎቹም የኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪካቸው በዚሁ አብቅቷል። አንዳንዶቹ አትሌቶች በግላቸው መሳተፍ ቢፈልጉም ሀገራቸው ስለከለከለቻቸው በከፍተኛ የስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ አልፈዋል።
ይህ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በስፖርቱ ውጤት ላይም ትልቅ ጥላ ጥሏል። በአንዳንድ ስፖርቶች ለምሳሌ እንደ ሆኪ እና የፈረስ ስፖርት የመሰሉ ውድድሮች ላይ ጥቂት ሀገራት ብቻ ስለተሳተፉባቸው፣ በወቅቱ አሸናፊ የነበሩት አትሌቶች ዛሬም ድረስ በታሪክ ፊት "እውነተኛ ሻምፒዮን" ለመባል አልታደሉም። ይህም የሚያሳየው ፖለቲካ ወደ ስፖርት ሜዳ ሲገባ ውጤቱ ድል ሳይሆን የአሸናፊዎችን ክብር ማሳነስ እና የተወዳዳሪዎችን ተስፋ መቁረጥ መሆኑን ነው።
የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ስጋት
በስፖርት ታሪክ ውስጥ የማግለል እርምጃዎች እንደ ሰንሰለት ተያያዥነት ያላቸው መሆናቸውን የ1984ቱ የሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ትልቅ ማሳያ ነው። አሜሪካ ለመራችው የ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ ማግለል አጸፋ ለመመለስ፣ ሶቪየት ህብረት እና 14 የኮሙኒስት ሀገራት ከሎስ አንጀለስን ውድድር ራሳቸውን አግልለዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በ1988ቱ የሴኡል ኦሊምፒክ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶቪየት ህብረት ጎራ የነበሩ ሀገራት ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለው ነበር። ይህ የቆየ የፖለቲካ ቁርሾ እና የማግለል አባዜ በ1992ቱ የባርሴሎና ኦሊምፒክ ላይ ነው መፍትሄ አግኝቶ ዓለም በአንድነት የታየችበት ታላቅ መድረክ ለመሆን የበቃው።
ከዓመታት በኋላ ቻይና የቤጂንግ ኦሊምፒክን ባሰናዳችበት ወቅት በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ጥያቄዎች ምክንያት የማግለል ጭምጭምታዎች ተሰምተው የነበረ ቢሆንም፣ ሀገራቱ ግን ሳይገፉበት ቀርተው ዓለም ድንቅ የተባለውን የ"በርድስ ኔስት" ትእይንት በአንድነት ለማየት በቅታለች።
በአጠቃላይ ሀገራት በትልልቅ የስፖርት መድረኮች ላይ የሚያደርጉት ማግለል ትልቁን ጉዳት የሚያደርሰው በአትሌቶች ላይ ነው። አትሌቶች ዕድሜያቸው ከሚፈቅደው የብቃት ጣራ በላይ ስለሚሆኑ፣ በፖለቲካ ምክንያት አንድን ውድድር ሲያልፉ ዳግም የመወዳደር ዕድል ላያገኙ ይችላሉ። ከሜዳሊያ እና ከዝና ባለፈም፣ የስፖንሰርሺፕ እና የፋይናንስ ገቢያቸው ይቋረጣል። አዘጋጅ ሀገራትም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሲያጡ፣ አግላይ አገራት ደግሞ በዲፕሎማሲው መድረክ "ስፖርትን ለፖለቲካ መሣሪያነት ይጠቀማሉ" የሚል ከፍተኛ ትችት ይደርስባቸዋል። ከዚህም በላይ የውድድሩ ተዓማኒነት በእጅጉ ይቀንሳል። ለምሳሌ በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ እንደ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ጀርመን ያሉ የአውሮፓ ታላላቅ አገራት የማይሳተፉ ከሆነ፣ አሸናፊው ቡድን የሚቀዳጀው "የዓለም ሻምፒዮን" የሚለው ስም ክብደትና ሙሉ ተቀባይነት እንዳይኖረው ያደርገዋል።
ከእነዚህ የታሪክ ትምህርቶች የምንረዳው ዋነኛው እውነታ፣ ማንኛውም ዓይነት የ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ማግለል ከተከሰተ ትልቁን ዋጋ የሚከፍለው ስፖርቱ እና ተጫዋቾቹ መሆናቸውን ነው። ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ለአፍታ የዲፕሎማሲ ድል ቢመስሉም፣ በስፖርቱ እና በከዋክብቱ ህይወት ላይ ግን የማይጠገን ጉዳት ጥለው ያልፋሉ።
የፊፋ ህልውና በፈተና ላይ፦ የማግለል ዛቻዎች እና የኢኮኖሚ ውድቀት ስጋት
በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ዙሪያ እያንዣበቡ ያሉ የማግለል ዛቻዎች እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ላይ ሊያመጡ የሚችሉት አደጋ ከቀላል ስፖርታዊ መስተጓጎል ባለፈ ተቋሙን እስከማፍረስ ወይም ክብር እስከማጣት ሊያደርሱት ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ ስጋቶች እውን የሚሆኑ ከሆነ፣ ፊፋ በታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ ሰፊ የህልውና አደጋ እንደሚጋረጥበት መገመት አዳጋች አይደለም።

ከእነዚህም መካከል ዋነኛው የገንዘብ ቀውስ ሲሆን፣ የፊፋ የገቢ ምንጭ ከ90 በመቶ በላይ የሚገኘው ከዓለም ዋንጫ የቲቪ ስርጭት መብት፣ ከስፖንሰርሺፕ እና ከቲኬት ሽያጭ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። እንደ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ፈረንሳይ ያሉ ትልልቅ ገበያ ያላቸው አገራት ውድድሩን ቦይኮት ካደረጉ፣ እንደ አዲዳስ ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የንግድ ገጽታችን ይበላሻል በሚል ስጋት ስምምነታቸውን ሊያቋርጡ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የቲቪ ስርጭት መብት የገዙ ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት ውድድሩ ጥራቱን ካጣና ምርጥ ተጫዋቾች ካልተሳተፉ ፊፋን በቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊከሱት ይችላሉ። ይህም ፊፋን በቀጥታ ወደማይወጣው የኢኮኖሚ ውድቀት ሊመራው ይችላል።
ተቋማዊ ተአማኒነት
ፊፋ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚታወቅበትና የሚመራበት ዋነኛው መርህ "እግር ኳስ ዓለምን አንድ ያደርጋል" የሚል ቢሆንም፣ አሁን ያለው የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረት ግን ይህንን ተቋማዊ ተአማኒነት አደጋ ላይ ጥሎታል። ፊፋ ለአሜሪካ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያደላ ወይም የዋሽንግተንን ተጽዕኖ መቀልበስ ያቃተው መስሎ ከታየ፣ እንደ አውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ያሉ አህጉራዊ ማህበራት በተቋሙ ላይ ያላቸው እምነት መሸርሸሩ አይቀሬ ነው።
በቅርቡ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር የአሜሪካን የኢሚግሬሽን ፖሊሲ እና የፖለቲካ አካሄድ በመቃወም ደጋፊዎች ወደ አሜሪካ እንዳይሄዱ ጥሪ ማቅረባቸው፣ በተቋሙ ከፍተኛ አመራርና በአባላት መካከል ያለውን ጥልቅ ክፍፍል ይበልጥ አጉልቶ አሳይቷል።
ይህንን ተከትሎ የሚመጣው ትልቁ ስጋት ፊፋን የሚተካ ወይም ከፊፋ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሌላ ዓለም አቀፍ ስብስብ ሊፈጠር ይችላል የሚለው ነው። ይህ ስጋት መሰረት የሌለው ሳይሆን በታሪክ የታየ እውነታ ነው። ለምሳሌ በ1976ቱ የሞንትሪያል ኦሊምፒክ ወቅት ውድድሩን ያገለሉ ሀገራት በጋራ በመሆን ለአትሌቶቻቸው ማካካሻ የሚሆን ተለዋጭ ውድድር በምዕራብ ጀርመን አዘጋጅተው ነበር። በወቅቱ እነ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ስፖርተኞች የተሳተፉበት ያ ውድድር፣ ኋላ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ረገበ እንጂ የመደገም ዕድል አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ዓለም ሁለት የተለያዩ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ይኖሯት ነበር።
በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ ያንዣበበው ጥላም ተመሳሳይ አደጋን ያዘለ ነው። ፊፋ በአባላቱ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ካልቻለ እና ውድድሩ በፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት ከተበላሸ፣ ሀገራት የራሳቸውን ዓለም አቀፍ ስብስብ ለመፍጠር መነሳሳታቸው አይቀሬ ነው። ይህም ፊፋን እንደ አንድ ወጥ ዓለም አቀፍ ተቋም የመቀጠል አቅሙን የሚፈትን ትልቅ አደጋ ሲሆን፣ ውጤቱም የስፖርቱን አንድነት አፍርሶ ዓለምን ወደ ተከፋፈለ የእግር ኳስ አስተዳደር ሊመራው ይችላል።
ተቋማዊ ክብሩን የማስጠበቅ ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው ፊፋ
የፊፋ ዓለም አቀፋዊ ህልውና የተመሰረተው በሁለት አበይት ምሶሶዎች ማለትም በአባል ሀገራት "አንድነት" እና ከዓለም ዋንጫ በሚገኝ "ገቢ" ላይ ነው። ሆኖም አሁን ላይ የሚሰሙት የማግለል ወይም የቦይኮት ዛቻዎች እነዚህን ተቋሙ የቆመባቸውን መሰረቶች በአንድ ጊዜ የማፍረስ አቅም አላቸው። በ2026ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ ያንዣበበው ይህ ስጋት ስፖርታዊ ውድድር ከመስተጓጎሉ ባለፈ፣ ፊፋ እንደ አንድ ትልቅ ዓለም አቀፍ ተቋም የመቀጠል አቅሙና ብቃቱ በጽኑ የሚፈተንበት የታሪክ አጋጣሚ ሆኗል።

ማንኛውም ዓይነት የማግለል ውሳኔ በተግባር ከተተረጎመ፣ ተቋሙን ወደ ከፋ የገንዘብ ቀውስ ከመክተቱም በላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል። የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ ስፖርቱ ሜዳ ሰርገው በገቡ ቁጥር ፊፋ አባላቱን አስተባብሮ የመያዝ አቅሙ እየመነመነ ይሄዳል፤ ይህም ውሎ አድሮ የስፖርቱን አንድነት የሚንድና ተቋሙን ለውድቀት የሚዳርግ ትልቅ አደጋ ነው። በአጠቃላይ በ2026 የሚታየው ጥላ ፊፋ የገቢ ምንጩንና ተቋማዊ ክብሩን ለማዳን በዲፕሎማሲው ረገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለበት የሚያሳስብ ቀይ መብራት ነው።
በንዋይ ይመር
#EBC #ebcdotstream #FIFA #worldcup #worldcup2026