Search

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በይፋ አስጀመሩ

ረቡዕ ጥር 27, 2018 112

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበር ለተደራጁ 6 ሺህ 194 የከተማዋ መምህራን የመኖሪያ ቤት ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ መምህራን ለረጅም ዓመታት ሲያነሱት ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ቀዳሚ ለሆነው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ነው።
በዛሬው ዕለትም በ57 ማኅበራት ተደራጅተው የቤቱን ዋጋ 25 በመቶ ለቆጠቡ መምህራን የሚገነቡት ቤቶች በከተማዋ በተለያዩ ሳይቶች ግንባታቸው ተጀምሯል።
ከተማ አስተዳደሩ ለግንባታው የሚውል በወቅታዊ ዋጋ 24 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ 40 ሄክታር መሬት በነፃ ያቀረበ ሲሆን፤ በተጨማሪም አስተዳደሩ ለቦታው 5 ቢሊዮን ብር የካሳ ግምት መክፈሉ ተገልጿል።
ይህ እርምጃ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ለጀመረችው ሥራ የቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ ተናግረዋል።
መምህራን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ መሆናቸው የተረጋጋ ሕይወትን በመምራት፣ የትውልድና የሀገር ግንባታ የዕውቀት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እንደሚያስችላቸውም አክለዋል።
በቀጣይ ከመምህራን በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞችም ተደራጅተው እየተጠባበቁ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ጥያቄያቸውን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የቤት ግንባታው የተጀመረላቸው መምህራንም በበኩላቸው፤ የተሰጠው ተግባራዊ ምላሽ ትውልድ የማነጽ ሥራቸውን ይበልጥ በተነሳሽነትና በዝግጅት እንዲያከናውኑ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በይመር አደም