Search

የነገዋ ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ፦ “እኛ ሠርተን ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር እናስረክብ”

ሓሙስ ጥር 28, 2018 103

ኢትዮጵያ ዛሬ በሕፃናት እና ወጣቶች ላይ የምታፈስሰው መዋዕለ ንዋይ ተራ የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ የነገዋን ብልጽግና የምታረጋግጥበት የትውልድ ኢንቨስትመንት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት፣ የመደመር እሳቤ ዋና ግብ ትላንት የተሰበሩትን ማረም፣ ዛሬ ያሉትን መልካም ነገሮች ማስፋፋት እና ነገ ላይ አዳዲስ እሴቶችን መጨመር ነው።

ይህ እሳቤ በሕፃናት እና ወጣቶች የወደፊት ተስፋ ላይ እንዴት እየተተገበረ እንደሆነ እና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር ያለውን ትርጉም በዝርዝር እንመልከተው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸውም ላይ እንዳሰመሩበት፣ የመደመር መንገድ የጀመረው ሪፎርም ቀዳሚ ዓላማ የዛሬው ድህነት እና የትላንትናው ዕዳ ወደ ልጆቻችን እንዳይሸጋገር ማድረግ ነው።

መደመር ማለት ትናንት የነበረውን ጉድለት ለነገ ማስተላለፍ ሳይሆን፣ ዛሬ ላይ ዕውቀትን እና ቴክኖሎጂን በመደመር የነገውን ስብራት ቀድሞ መከላከል ነው።

እንደ ኖርዌይ እና ሲንጋፖር ያሉ ሀገራት የዛሬውን ቁሳዊ ሀብታቸውን ለነገው ትውልድ ያስቀምጣሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ በሰው ሀብቷ ላይ በማተኮር፣ አዕምሮው በዕውቀት የለማ እና ለውድድር ብቁ የሆነ ትውልድን ለነገ እያስቀመጠች ነው።

በዚህ ረገድ እየተተገበሩ ካሉ ሥራዎች መካከል የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ እና ከመሠረታዊ ትምህርት እስከ ሳይንስ ሙዚየም ይጠቀሳሉ።

የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ የወጣቶቻችንን አቅም ከዓለም አቀፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር የሚያስተሣሥር የዕውቀት መደመር ማሳያ ነው።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ወጣቶቿን በኮዲንግ ዕውቀት በማስታጠቅ፣ ይህንን ኃይል ወደ ኢኮኖሚ ሞተርነት እየቀየረች የምትገኘው።

ሕንድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶቿን በዲጂታል ዕውቀት በማስታጠቋ ዛሬ የዓለም የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን ችላለች።

ኢትዮጵያም ይህንን ዓለም አቀፍ ስኬት ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዳበል ወጣቶቿን ለነገው የሥራ ገበያ እያዘጋጀች ነው።

በመደመር ፍልስፍና፣ ትልቅ ሕንፃ ከመገንባት ይልቅ ትውልድ መገንባት ይቀድማል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት 34 ሺህ መዋዕለ ሕፃናት የተገነቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ትልቁ ተስፋዎች የሆኑ 4 ሚሊዮን ሕፃናት በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ሳይንስ ሙዚየም እና ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ ድረስ የምታከናውናቸው ሥራዎች፣ ሕፃናት በሳይንስ እና በጥበብ ታንፀው እንዲያድጉ ታላቅ መሠረት እየጣሉ ነው።

መደመር ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ቀጣናዊ ራዕይም አለው። አፍሪካ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚኖራትን 1.1 ቢሊዮን ወጣት ኃይል፣ ኢትዮጵያ እንደ ትልቅ ዕድል ትመለከተዋለች።

የወጣቶቻችን ዕውቀት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሲደመር፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብልጽግና ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እና የሰላም ተምሳሌት እንድትሆን ያስችላታል።

የመደመር እሳቤ “እኛ ሠርተን ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር እናስረክብ” የሚል ጥልቅ ቃልኪዳን ነው።

ዛሬ የምንዘራው የዕውቀት፣ የሰላም እና የቴክኖሎጂ ዘር ነገ በልጆቻችን ሕይወት ላይ የብልጽግና ፍሬ ሆኖ ይፈካል።

በለሚ ታደሰ