በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የአስረጂ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ኮሪያ መንግሥታት በጤናው ዘርፍ ያለውን የመሠረተ ልማት እጥረት ለመቅረፍ በማለም የተፈራረሙት የ30 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ማስፈፀሚያ የሚውለው ፋይናንስ፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ 75 ጤና ጣቢያዎች፣ 24 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እና 129 የቀዶ ጥገና ክፍሎችን በዘመናዊ መሣሪያዎች ለማደራጀት ያለመ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ እንደገለጹት፣ ከደቡብ ኮሪያ ኤክስፖርት - ኢምፖርት ባንክ የተገኘው ብድር እጅግ ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበትና በ40 ዓመታት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።

ፕሮጀክቱ ከመሣሪያ አቅርቦት ባለፈ የባለሙያዎችን የጥገና እና የሕክምና መሣሪያዎች አጠቃቀም አቅም ለመገንባት የሚሠራ ሲሆን፣ በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የግብዓት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውለው የብድር ስምምነት የጤና ተቋማትን የሕክምና ግብዓት እጥረት ለመፍታት ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
በሞላ ዓለማየሁ