የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት መጠናቀቅ እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጀመር የኢትዮጵያን ገፅታ እንደ አዲስ የሚያስተዋውቁ መሆናቸውን የምጣኔ ሀብት ባለሞያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ገለፁ።
በሀገራችን እየተሰሩ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት አቶ ዘመዴነህ፤ ለሀገሪቱ የከፍታ ጉዞም መሰረት እንደሆኑ ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የውጭ ምንዛሬን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ መሆኑን አንስተው፤ ፕሮጀክቶችን በዕቅድ ይዞ በተግባር መጨረስን ከቃል ባለፈ በተግባር ያየንበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዕምቅ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ነገር ግን ባላት ሀብት ልክ መጠቀም ሳትችል መቅረቷን አቶ ዘመዴነህ ጠቅሰዋል፡፡
ከሰሞኑ የተመረቀው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለተፈጥሮ ሀብት ትኩረት ተሰጥቶት ስራ ላይ ማዋል እንደተቻለ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ማደግ ለቀጣናው ሀገራት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና የተጀመሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንደምንችል በተግባር ያየንበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምትሰራቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች የመንግስት እና የግል ተቋማት በጋራ የሚሰሩበትን ሂደት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ተናግረዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Natural_gas #Mega_Projects
በሔለን ተስፋዬ