የኢሬቻ ሆረ ሀርሰዲ ‘የኢሬፈና’ /ምስጋና የማቅረብ/ ሥነ-ሥርዓት በአባገዳዎች መሪነት በቢሾፍቱ ከተማ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይጀመራል።
ቢሾፍቱ ከተማ እና ሆረ ሀርሰዲም ተውበው የበዓሉ ታዳሚዎችን የተቀበሉ ሲሆን ታዳማዊዎቹም በባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው ከዋዜማው ጀምሮ በምስጋና እና በጭፈራ ለሥነ-ሥርዓቱ ሲዘጋጁ ቆይተዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ አበገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎች፣ ቀሬዎች፣ ሁሉም እንደየደረጃቸው የክረምቱ ጭጋግ መገፈፉን፣ ፈጣሪያቸው ምሕረት ማድረጉን፣ ከዘመን ዘመን ማሸጋገሩን ያበስራሉ።

በኢሬቻ በዓል እናቶች እና አባቶች፣ ቄሮ እና ቀሬዎች ለምለም ሳር እና አደይ አበባ ይዘው “መሬ ሆ…!” እያሉ በታላቅ እልልታ ምስጋና ያቀርባሉ።
ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከጥንት ቅድመ አያቶቹ ጀምሮ ሕዝቡ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት እና ሰላም የሚያጠናክርበት፣ ይቅርታ እና እርቅ የሚፈፀምበት በዓል ነው።
እንኳን አደረሳችሁ!