የቻይናው ኢንቪዥን ኩባንያ በየዓመቱ 320 ሺህ ቶን አረንጓዴ ሃይድሮጂን ማምረት የሚችለውን ኢንዱስትሪ ሥራ መጀመሩን ይፋ አደረገ፡፡
አረንጓዴ የኃይል ምንጭ ነው የተባለውን የሃይድሮጅን አሞኒያ ምርትን በ2028 በዓመት እስከ 1.5 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል።
ምርቱ ቻይና በአሁኑ ጊዜ ለኢንዱስትሪዎቿ እየተጠቀመችበት ያለውን ካርቦን አመንጭ የኃይል ምንጮችን ለማስወገድ እና በአረንጓዴ የኃይል ምንጭ ለመተካት እያደረገችው ያለውን ከፍተኛ ጥረት ይደግፋል ተብሏል።
ዋና መሥሪያ ቤቱ ሻንጋይ የሚገኘው ኢንቪዥን የአረንጓዴ ሃይድሮጂን ምርት የመጀመሪያ ምዕራፍ በሞንጎሊያ ቺፌንግ ውስጥ ነው ያስጀመረው።
ይህ በመጀመሪያ ምዕራፍ የተገነባው የሃይድሮጂን አሞኒያ መምረቻ በየዓመቱ 320 ሺህ ቶን የንጹህ ኃይል የሆነውን አረንጓዴ ሃይድሮጂን ማቅረብ የሚችል መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል።
የዚህ ሥራ መሳካት ከቴክኖሎጂ ስኬት በላይ መሆኑን የኢንቪዥን መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር ዛንግ ሌይ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለውም፣ "እያደገ የሚሄደው አረንጓዴ ኃይል አማራጭ እውን ሆኗል፤ ያለ አረንጓዴ ሃይድሮጅን ወደ ዜሮ ካርቦን መድረስ አንችልም፤ ይህን የመጻኢ ጊዜ የኃይል ምንጭ ለማሳካት ደግሞ የምንጠብቀው ጊዜ የለም" ማለታቸውን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ዘግቧል፡፡
#EBC #EBCdotstream #greenenergyrevolution #greenhydrogenplant