የሕዝብ ድምፅ የሆነው ኢቢሲ በሀገሪቱ የሚከናወኑ የልማት፣ የዲሞክራሲ፣ የሰላም እና የሰብዐዊ መብት ጥበቃ ሥራዎችን ከመንግሥት ወደ ሕዝብ ከሕዝብ ወደ መንግሥት የማስተላለፍ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ሲሉ በኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ ገልፀዋል።
አቢሲ በምክር ቤቱ ውስጥ የሚካሄዱ ስብሰባዎች፣ ክርክሮች፣ ውይይቶች፣ የሕግ ምርመራዎች፣ የሚወጡ አዋጆችና መደበኛ የመንግሥት ሪፖርቶች ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ መረጃዎችን እያስተላለፈ መሆኑንም አንስተዋል።
ከአንጋፋው ብሔራዊ ሚዲያ አቢሲ ጋር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለየ ትስስር እንዳለው የተናገሩት አቶ አዝመራ፥ እነዚህ መረጃዎችን በስፋት ወደ ህዝቡ ለማድረስ የአየር ሰዓት አጥረት በመኖሩ የፓርላማ ቻናል መክፈቱ ጥቅሙ የጎላ ነው ብለዋል።
አቢሲ የፊታችን ሰኞ በይፋ የሚጀምረው የኢቲቪ ፓርላማ ቻናልም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚነሱ የመንግሥት ሥራዎች ላይ ግልፀኝነት እንዲኖር፣ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጠናከርና ማህበረሰቡ የራሳቸውን ግብዓት እንዲጨምሩ የሚያስችል መሆኑን አቶ አዝመራ ገልፀዋል።
ቻናሉ የ24 ሰዓታት አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ማኅበረሰቡ በሰብዐዊ መብት ጉዳዮች፣ በአዋጆች፣ በሪፖርቶች፣ በመንግሥት እቅዶች አፈፃፀም ላይ የሚወያዩበት፤ የቁጥጥርና ክትትል ግኝቶችም ለሕዝብ ይፋ የሚደረግበት ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ቻናሉ የሕዝብና የመንግሥት ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የወል ትርክት ግንባታ፣ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና የተቋም ግንባታ ላይ አቢሲ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ስለሆነም ሕዝቡ አቲቪ ፓርላማ ቻናልን በመከታተል ለመረጃ ቅርብ መሆን እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
በየተመኙሽ አያሌው