የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም እና ሁሉን አቀፍ ዕድገት እውን ለማድረግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የአጀንዳ እና የተሳታፊ ልየታ ሥራ ሲያካሂድ የቆየው ኮሚሽኑ፤ በበቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም "የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ በምክክሩ ሂደት ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር እየተወያየ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚሽነር ብሌን ገ/መድህን ኮሚሽኑ፥ ኮሚሽኑ ባሳለፋቸው የውይይት ምዕራፎች ለሀገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ የሆኑ ዋና ዋና ተግባራትን በስኬት አከናውኗል ብለዋል።
እስካሁን በተከናወኑት ሥራዎች ኅብረተሰቡ ያደረገው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ሕዝባዊ ተሳትፎው በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በኮሚሽኑ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ በቀጣይ በሚያካሂደው ሀገራዊ ምክክር ላይ ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በንቃት እንዲሳተፉ ያለመ ተመሳሳይ ውይይት በሐረሪ፣ በድሬዳዋ እና በሶማሌ ክልሎችም እየተካሄደ ነው ብለዋል።
በጀማል አህመድ