የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሪፎርም፣ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ እና የህንፃ ምረቃ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)፥ ፖሊስ የአሠራር ነጻነት እንዲኖረው እና ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ እንዲሆን መደረጉ ለለውጥ ሥራዎች መሠረት የጣለ እና ሠራዊቱ ሙያውን አክብሮ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ያስቻለ ነው ብለዋል።
ተቋማዊ ሪፎርሙን ተከትሎም የክልሉ ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ እያጋጠመ ያለው የፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ተግባር ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል ያሉት ዋና አዛዡ፤ ችግሩን በውስጥ አቅም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
"ፖሊስ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው እየተደረገ ያለው ጥረትም ለውጥ እያመጣ ነው" ብለዋል።
በሪፎርም ሥራዎች ቴክኖሎጂ መር ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ እንዲጠናከር እየተሠራ መሆኑንም ዋና አዛዡ ጠቁመዋል።
በሕግ ማስከበር ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው አባላትን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት፣ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ እና የፖሊስ ኮሌጅን ደረጃ ማሳደግ የክልሉ ፖሊስ የሪፎርም ሥራዎች አካል መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
ከ3 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የሹመት ዕድገቶች ይሰጣሉ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህም ለላቀ የግዳጅ አፈፃፀም እና መዋቅራዊ ሪፎርም መሳካት አጋዥ ነው ብለዋል።
በራሔል ፍሬው