Search

የመሶብ አገልግሎት መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

እሑድ መስከረም 25, 2018 44

የባህር ዳር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳደር አረጋ ከበደ፣ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ በተፈጥሮ የታደለችው ውቧ ባህር ዳር ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎት ይገባታል ብለዋል።
ማዕከሉ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ሀገር በቀል ከሆኑ የለውጥ ሀሳቦች የሚመደብ እና መንግሥት ማኅበረሠቡ የሚያነሳውን የአገልግሎት መጓደል በማረም ለሕዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ወደ ሕዝቡ እንዲቀርብ ከከተሞች ቀጥሎ ቀበሌዎች ፈጥነው ለውጡን መቀላቀል እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል።
የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የሕዝብ እርካታን ለማሳደግ እና የመንግሥትን ቅቡልነት ማሻሻል የሚያስችል አገልግሎት የሚሠጥበት ተቋም መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ብልሹ አሠራሮችን ለመታገልም ተቋማትን ማጠናከር እና አሠራርን ማዘመን ላይ ትኩረት ሠጥተን እየሠራን ነው ብለዋል።
በባህርዳር ከተማ በተመረቀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ 12 ተቋማት 92 አገልግሎቶችን እንደሚያቀርቡ ተመላክቷል።
 
በራሔል ፍሬው