ሰንደቅ ዓላማ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ የታተመ የሀገራዊ አንድነት እና ነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ ነው።
ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር መንግሥት እና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሥልጣን፣ ነፃነት፣ ዕድገት እና ማኅበረሰባዊ ትሥሥር መፍጠሪያ መሣሪያ ነው።
ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 03 ቀን 2018 ዓ.ም “ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
የአንድነታችን እና የኅብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪዎችን አሸንፈው ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሕይዎት መሥዋዕትን ከፍለው ለአዲሱ ትውልድ አስረክበዋል።
ይህንኑ መሠረት በማድረግ ሰንደቅ ዓላማ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚከበር ታላቅ ሀገራዊ በዓል ነው።
በመሆኑም የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ክብር እና ተገቢውን ከፍታ አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን እና የግዛት አንድነትን ማስቀጠል፤ ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በማጽናት የሀገራችንን የዕድገት ከፍታ ማረጋገጥ ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።
የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በተለያየ መልኩ በየዓመቱ እየተከበረ 18 ዓመታትን አስቆጥሯል።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀንም በፌዴራል፣ በክልሎች አና በሁለቱም የከተማ አስተዳደር ከተሞች ከሰንደቅ ዓላማ መርሆዎች ጋር ተገናዝቦ እና የኢትጵያን ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራትና ማንሰራራት በሚያረጋግጡ ውይይቶች ታጅቦ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በመላው ሀገሪቱ ይከበራል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል መከበሩ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን በማስጠበቅ የኢትጵያን የከፍታ ብሥራት እና ሕዳሴ ለማረጋገጥ ለሀገር ክብር እና ጥቅም ሁሉም ዜጋ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃሉን የሚያድስበት ዕለት ይሆናል።
በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት፣ በክልሎች እና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎች እና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ የመፈፀም ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
#EBC #ebcdotstream #EthiopianFlag #flag #nationalflagday