Search

በመቀሌ አቅራቢያ 2 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ቅዳሜ ጥቅምት 01, 2018 74

በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 5 እና 5 ነጥብ 2 የተመዘገበ ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ሕዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ሣይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ገለጹ።
ፕሮፌሰር አታላይ፥ የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በመቀሌ አቅራቢያ በስምጥ ሸለቆና የደጋማው መገናኛ ጠርዝ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ 18 ደቂቃ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 5 እና ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ደግሞ 5 ነጥብ 2 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጦች መከሰታቸውን አስታውቀዋል።
በመቀሌ አቅራቢያ የተከሰቱት ሁለት ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችም በ17 ደቂቃ ልዩነት መሆኑንም አስረድተዋል።
ዛሬ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት አካባቢም የስምጥ ሸለቆ ቆላማና የደጋማው መገናኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከአሁን ቀደምም የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ የሚከሰትበት አካባቢ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።