Search

ጣሊያን የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት ትደግፋለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ

ጣሊያን የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት ትደግፋች ሲሉ የጣሊያን ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሚኒስትሮች ምክርቤት ፕሬዚዳንት ጆርጂያ ሜሎኒ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚንስትሯ በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጣሊያን መንግስት በአፍሪካ ሀገራት የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶችን ጥምረት በማጠናከር ኢንቨስትመንትን የሚስቡ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ጣሊያን የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ሉዐላዊነትን ለማረጋጋጥ ለሚያደርጉት ጥረት፤ ያላትን ልምድ በማጋራት ለመደገፍ ትሰራለች ሲሉም ተናግረዋል።

ይህንን ጥምረት በማጠናከር በርካታ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሯ፥ ለዚህም እንደ አብነት በአልጄሪያ 36 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 44 ሺህ ቶን ምርት ለማግኘት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ ጥረት በተመሳሳይ በሴኔጋል፣ጋና እና ኮንጎ እየተካሄደ ነው ያሉ ሲሆን፤ በቅርቡ ኮትዲቯር፣ ኬንያ እና ቱኒዚያም ልምዱን የማካፈል ሥራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

የጣልያን መንግሥት በአፍሪካ በተለያዩ አገሮች ውስጥ የቡና ምርት ላይ እገዛ በማድረግ እና የእሴት ሰንሰለቶችን ለማዘመንም ይረዳል ብለዋል።

ግባችን ጥገኝነትን መፍጠር አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሯ፥ ሀገራቱ የምግብ ሉዓላዊነታቸውን በማረጋጋጥ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች እንዲያስተዋውቁ ኢንቨስት በማድረግ ማገዝ ነው ብለዋል።

በሃይማኖት ከበደ