Search

ኢትዮጵያውያን በጋራ ታላላቅ ድሎችን የተቀዳጁበት የአንድነት ተምሳሌት - ሰንደቅ ዓላማ!

እሑድ ጥቅምት 02, 2018 163

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ ዕለት እንደሚከበር በአዋጅ ተደንግጓል።

ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበር እና ክብሯን ለማስጠበቅ ደም እና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩት የነፃነት ዓርማ ነው።

ኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት የነፃነት ተምሳሌት፣ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ድል ፋና ወጊ እና ነፃነታቸውን ለተነጠቁ የአፍሪካ ሀገራት እና ሌሎች ሕዝቦች የነፃነት ብርሃን ፈንጣቂ ሀገር ናት።

ይህ አኩሪ እና ድንቅ ገድል የተገኘውም ሕዝቦቿ ሰንደቅ ዓላማቸውን ከፍ በማድረግ በየዘመናት የገጠማቸውን ፈተና በድል በማለፍ፣ ሀገራዊ ጀብድ እና ዐርበኝነት በመፈፀማቸው ነው።

ኢትዮጵያውያን በጋራ ታላላቅ ድሎችን የተቀዳጁበት የአንድነት ተምሳሌት የሆነው ሰንደቅ ዓላማ በጋራ የሚከበርበት ታላቅ ብሔራዊ ቀን በአዋጅ ተደንግጓል።

ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ በዓል የሚከበርበት ዋና ዓላማም ለሰንደቅ ዓላማው የሚገባውን ክብር በመስጠት ዜጎች የጋራ ዕሴቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት እና በሀገራዊ አንድነት እና ኅብረ ብሔራዊነት መግባባትን የሚፈጥሩበት ሀገራዊ በዓል በመሆኑ ነው።

የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እና ሁነቶች ደምቆ መከበር ከጀመረ እነሆ 17 ዓመታትን አስቆጥሯል።

ዘንድሮም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት እና አስተባባሪነት ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ለ18ኛ ጊዜ በመላ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሀገራዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በድምቀት ይከበራል።

የበዓሉ መሪ ቃልም፣ "ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ' የሚል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል።

ዕለቱ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ዜጎች በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቆመው ቃለ መሃላ በመፈፀም ለሀገራቸው እና ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ክብር እና ፍቅር ዳግም የሚገልጹበት፤ የሀገራቸውን አንድነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ቃላቸውን የሚያድሱበት ዕለት ይሆናል።

የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች ስለ ሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ክብር እና ትርጓሜ በተገቢው መንገድ እንዲረዱ በማድረግ ረገድ የራሱ አስተዋፅኦ አለው።

ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን እና ለሉዓላዊነታችን መገለጫ፤ የኅብረ ብሔራዊነታችን የአብሮነታችን ማሳያ፤ የአንድነታችን የጋራ ዓርማ፤ የነፃነታችን እና የሉዓላዊነታችን ሕያው ምስክር ነው።

ሰንደቅ ዓላማችንን ስናከብር ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን እና ሌሎች ፀጥታ አካላት ዕውቅና እና ክብር መስጠት እንዲሁም ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ክብር እና ጥቅም የተከፈለውን መሥዋዕትነት ማሰብ አስፈላጊ ነው።

#EBC #ebcdotstream #EthiopianFlag #flag #nationalflagday