የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ "ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ' በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በክብ ሰማያዊ መደብ ላይ የተቀረፀ ብሔራዊ ዓርማ እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡
ብሔራዊ ዓርማው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑንም ያስቀምጣል፡፡
ዓርማው በሰንደቅ ዓላማው መካከል ላይ የሚያርፈው የክቡ ዙርያ የአረንጋዴውንና የቀዩን ቀለም ቁመት አጋማሽ አካል ሲሆን፤ እነዚህ ቀለማት አግድም የተዋቀሩና እኩል ስፋት የሚኖራቸው ሆኖ የሰንደቅ ዓላማው ወርድ የቁመቱን እጥፍ ይሆናል፡፡
ሰንደቅ ዓላማው ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረ ኮከብ የሚኖረው ሲሆን ቀጥታና እኩል በሆኑ መስመሮች መተላለፊያ ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ጨረር ይኖረዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማ ቀለማቱ ትርጓሜ
👉 አረንጓዴው፡- የስራ፣ የልምላሜና የዕድገት ምልክት
👉 ቢጫው፡- የተስፋ፣ የፍትሕና የእኩልነት ምልክት
👉 ቀዩ፡- ለነጻነትና ለእኩልነት መስፈን የሚደረግ የመስዋእትነትና የጀግንነት ምልክት
በሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ዓርማ ትርጓሜ
👉 ክብ ቅርፅ ያለው ሰማያዊ መደብ፤ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያንፀባርቅ ነው
👉 ቀጥታና እኩል የሆኑት መስመሮች፡- የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶች እኩልነትን ያመለክታል
👉 ቀጥታና እኩል ከሆኑ መስመሮች የተዋቀረው ኮከብ፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ የመሰረቱትን አንድነት ያመለክታል
👉 ቢጫ ጨረር፤ በመፈቃቀድ አንድነት ለመሰረቱት ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ክብር መጠበቅና ብሔራዊ ዓርማውን ማክበር የዜጎችን እኩልነትና በመከባበር አብሮ ለመኖር የገቡትን ቃልኪዳን ማክበር ነው።
በሔለን ተስፋዬ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #National_flag_day