“አዲሱ ባሕር ኃይል ቦታውን ሲይዝ አብሬ እጓዛለሁ፤ በዚያም በትምህርት እና በልምድ ያገኘሁትን ዕውቀት ሕይወቴ እስከሚያልፍበት ዕለት ድረስ ሳካፍል እቆያለሁ” ሲሉ የቀድሞው ባሕር ኃይል አባል ማስተር ቺፍ ገረመው ኃይሌ ይናገራሉ።
“የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ፈረሰ ሲባል ስሰማ ወላጆቼ በሞት ሲለዩኝ ካዘንኩት በበለጠ ነበር የከፋኝ” የሚሉት ማስተር ቺፍ ገረመው፤ በተለይ ሀገራችን የቀይ ባሕር ተጠቃሚነቷ ተነጥቆ ማየት ለእኔም ሆነ ለባልደረቦቼ የቁም ሞት ነበር ሲሉ ይገልጻሉ።
ሆኖም የልብ እና የታሪክ ስብራታችንን የሚያክመው “የባሕር በር ያስፈልገናል” የሚለው አቋም መጽናኛ እንደሆናቸው ማስተር ቺፍ ገረመው ከኢቢሲ የእሁድ ቤት መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በቀድሞው ባሕር ኃይል ለ31 ዓመታት ያገለገሉት ማስተር ቺፍ ገረመው የ18 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር ባሽር ኃይሉን የተቀላቀሉት።
ለሙዚቃ ትልቅ ፍቅር እንዳላቸው ጠቅሰው በወቅቱ የባሕር ኃይል አባላት ከዋናው ሥልጠና በተጨማሪ የሙዚቃ ትምህርት ይሰጣቸው ስለነበር እነርሱን የመቀላቀል ፍላጎት እንዳደረባቸው ይገልጻሉ።
እንደዚያ የጀመረው የባሕር ኃይል አባልነት ሕይወታቸው በማይዘነጉ በርካታ አስተማሪ እና አዝናኝ ትውስታዎች እና ትዝታዎች የተሞላ ስለመሆኑ ያወሳሉ።

የኢትዮጵያ መርከብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ እያውለበለበ ከብዙ በጥቂቱ ኖርዌይ፣ ኢራን፣ ታይላንድ፣ ማዳጋስካር እና ህንድ ድረስ ይጓዝ እንደነበርም ይገልጻሉ። በዚህም ኢትዮጵያን በክብር ያስተዋውቅ እንደነበር በቁጭት ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ የእዚያ ዘመን ኃያልነቷ እንዲመለስ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት እና እያከናወነው ያለውን ሥራ ያደንቃሉ።
ከቀድሞው ባሕር ኃይል ያካበቱትን ዕውቀት እና ልምድ በማካፈል የመንግሥት እና ሕዝብን ጥረት ለማገዝ ያላቸውን የወትሮ ዝግጁነትም አረጋግጠዋል የቀድሞው ባሕር ኃይል አባል ማስተር ቺፍ ገረመው ኃይሌ።
በአፎሚያ ክበበው
#ebcdotstream #etv #ethiopia #redsea #ethiopiannavy