የብሔራዊ መዝሙር ታሪክ ከሀገር ምሥረታ፣ ከሀገራዊ ብሔርተኝነት መቀስቀስ እና ከዘመናዊ ብሔራዊ መንግሥታት ምስረታ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡
ብሔራዊ መዝሙር በዋነኛነት እንደ ባህል የተስፋፋውበ18ኛው እና 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በነበሩትአብዮቶች፣ ሪፐብሊክ ምሥረታ እና የሀገራዊ ብሔርተኝነት ስሜት ቢሆንም ጥቂት ሀገራት ቀድሞም ቢሆን እንደ ብሔራዊ መዝሙር የሚቆጥሩአቸው መዝሙሮች ነበሩአቸው።
ፈረንሣይ የመጀመሪያዋ በአዋጅ ብሔራዊ መዝሙርን ያፀደቀች ሀገር ስትሆን፣ በ1795 "ላ ማርሴላይዝ" የተሰኘውን መዝሙሯን ይፋ አድርጋለች። "ላ ማርሴላይዝ" ብሔራዊ መዝሙር ሆኖ በአዋጅ ከመጽደቁ በፊት በ1792 "የራይን ጦር የጦርነት ዘፈን" ተብሎ ተቀናብሮ የፈረንሣይ አብዮት መንፈስ እና የሀገር ፍቅር መቀስቀሻ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል።
የሀገራት ብሔራዊ መዝሙራት ውስጣዊ ቀውሶችን ወይም የእርስ በርስ ጦርነትን(ለምሳሌ አሜሪካ)፣ ነፃነትን ወይምአብዮትን(ለምሳሌ ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ)፣ ለነገሥታትክብር(ዩናይትድ ኪንግደም)፣ አንድነት፣ ታሪክ እና ቅርስን(ጃፓን)እና የድህረ-ቅኝ ግዛት ማንነትን(የአፍሪካ ሀገራት) የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሀገራት ለነገሥታቶቻቸው ክብር ነበር ብሔራዊ መዝሙር የሚዘምሩት፡፡ እ.ኤ.አ. በ1745 የተደረሰው እና "እግዚአብሔር ንጉሱን/ንግሥቲቱን ያድናል"የሚለው የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ መዝሙር ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ብሔራዊ መዝሙር እንደሆ ይነገራል።
ኔዘርላንድስ(1568) ፣ ዩናይትድ ኪንግደም(1745) ፣ ስፔን(1770) ፣ዴንማር(1780) እና ፈረንሳይ(1795) ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ብሔራዊ መዝሙራት ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡
"ላ ማርቻ ሪል" ወይም "ሪ(ሮ)ያል ማርች" የተሰኘው የስፔን ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ከሌላቸው ጥቂት ብሔራዊ መዝሙሮች አንዱ ነው። በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረው ዜማ የስፔን አንድነት እና ኩራት ምልክት ነው። ግጥም አልባነቱበተለያዩ የስፔን ክልሎች ውስጥ የቋንቋ መሰናክሎችን አልፎ ተወዳጅ እና የብሔራዊ ኩራት ምልክት እንዲሆን አስችሎታል።
የብሔራዊ መዝሙር ታሪክ በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በሦስት ሥርዓቶች ሦስት የተለያዩ ብሔራዊ መዝሙሮችን አስተናግዳለች። የመጀመሪያው መዝሙርበኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመን የነበረው ሲሆን፣ በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ግጥም ደራሲነት፣ በአርመናዊው ሙዚቀኛ ኬቮርክ ናልባንዲያን ዜማ ደራሲነት የተቀናበረ ነበር።የመዝሙሩ ግጥሞችም፡
ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣
በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ፣
ተባብረዋልና አርበኞችሽ፣
አይነካም ከቶ ነፃነትሽ፣
ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ፣
አትፈሪም ከጠላቶችሽ።
ድል አድራጊው ንጉሣችን፣
ይኑርልን ለክብራችን። የሚል ነበር፡፡
ሁለተኛው መዝሙር "ኢትዮጵያ ቅደሚ" የሚለው ሲሆንበኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደርደርግ፣ ቀጥሎም በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊሪፐብሊክ በአገልግሎት ላይ ውሏል።
“ኢትዮጵያ ቅደሚ” የተሰኘው መዝሙር ግጥሙ በአሰፋ ገብረማርያም ተጽፎ ዜማው በዳንኤል ዮሐንስ ተደርሶለት የተዘጋጀ ነበር። ግጥሙም፡-
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ -ኢትዮጵያ ቅደሚ፣
በኅብረተሰባዊነት - አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል - ጀግኖች ልጆችሽ፣
ወንዞች ተራሮችሽ - ድንግል መሬትሽ፣
ለኢትዮጵያ አንድነት - ለነፃነትሽ፣
መስዋዕት ሊሆኑ - ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጂ ወደፊት - በጥበብ ጎዳና፣
ታጠቂ ለሥራ - ላገር ብልጽግና!
የጀግኖች እናት ነሽ - በልጆችሽ ኩሪ፣
ጠላቶችሽ ይጥፉ - ለዘላለም ኑሪ።
የሚል ነበረ፡፡
በ1984 ዓ.ም ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ አዲስ የሕዝብመዝሙር በደረጀ መላኩ ገጣሚነት፣ በሰሎሞን ሉሉ ዜማደራሲነት የወጣው "የዜግነት ክብር" የተኘው ነው። ይህ መዝሙር በብዙዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያንፀበርቅ እና በብዙዎች የሚወደድ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ በሥራ ላይ ያለ ነው፡፡ የመዝሙሩ ግጥምም፡-
የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ፣
ታየ ሕዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ፤
ለሰላም ለፍትሕ ለሕዝቦች ነፃነት፣
በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት፤
መሰረተ ፅኑ ስብዕናን ያልሻርን፣
ሕዝቦች ነን ለሥራ በሥራ የኖርን፣
ድንቅ የባህል መድረክ ያኩሪ ቅርስ ባለቤት፣
የተፈጥሮ ፀጋ የጀግና ሕዝብ እናት፤
እንጠብቅሻለን አለብን አደራ፣
ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ።