የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኀበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሰንደቅ ዓላማ የሀገርን ሀሳባዊ ትዕምርት የሚያንፀባርቅ መለያ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገር አንድም በወሰን ድንበሯ የሚጨበጥ ስትሆን በሰዎች ሀሳባዊ እይታ እና የእኔነት ስሜት ደግሞ ሀሳባዊ መሆኗን ያስረዱት ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ፤ ሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ይህን ሀሳባዊ ትዕምርት የሚገልፅ ነው ብለዋል።
ሰንደቅ ዓላማ በርካታ ሃሳቦችን በአንድ የገመደ መሆኑን አንስተው፤ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ዜጎች ዓድዋ ላይ የመጣ ጠላት እኔ ዘንድ እንደመጣ ይቆጠራል ብለው መዝመታቸው የሀገርን ሀሳባዊነት በግልፅ ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።
የሀገር ሀሳባዊ እይታ የሀገርን ምንነት፣ በውስጧ የያዘችውን ታሪክ እና እውነት፣ ለማን እየሰራን እና ለማን ዋጋ እየከፈልን እንዳለን የሚያሳየን መስታወት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
ከቀለማት ስብጥር ያለፈ ትርጉም ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በዘመናት ውስጥ ያለፍናቸውን የድል መንገዶች የሚያሳይ ብሎም ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ሰንደቅ አላማ ቀለማት ምስረታ ፈር የቀደደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰንደቅ አላማ ከሀገር ሉዓላዊነት እና ነፃነት ጋር የተገናኘ እንደመሆኑም ለሰንድቅ ዓላማ የሚሰጠው ክብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሴራን ታደሰ