Search

“ጋዛን ብጎበኝ ክብር ይሰማኛል፤ ምድሩን ብረግጥ ደስ ባለኝ ነበር” - ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ሰኞ ጥቅምት 03, 2018 64

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራዔል፣ ቴል አቪቭ ናቸው።
ፕሬዚዳንቱ ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የእስራዔሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ቀዳማዊት እመቤት ሳራ ኔታንያሁ፣ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እንዲሁም የፕሬዚዳንት ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋዛን የመጎብኘት ሐሳብ ይኖራቸው እንደሆነ ተጠይቀው “ያንን ባደርግ ክብር ይሰማኛል፤ ሳልጎበኘውም በደንብ አውቀዋለሁ፤ ምድሩን ብረግጥ ደስ ባለኝ ነበር” ብለዋል።
ቀጥለውም፣ “በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት ታላቅ ተዓምር ይፈጠራል፤ በእጅጉ ፈጥነህ የምትሄድ ከሆነ ነገሮች ልክ አይሆኑም፤ በተገቢው ፍጥነት ነው መሔድ ያለብህ” ሲሉ አክለዋል።
በሌላ በኩል፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራዔላውያን ታጋቾችን በማስለቀቃቸው ከፍተኛ የእስራዔል ፕሬዚዳንታዊ የክብር ሜዳሊያ እንደሚሰጣቸው የፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ ጽ/ቤት አስታውቋል።
የእስራዔሉ ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ ዛሬ ለፕሬዚንት ትራምፕ የክብር ሜዳሊያውን እንደሚሰጧቸው እንደሚያሳውቁ እና ዶናልድ ትራምፕም ሜዳሊያውን በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ በይፋ እንደሚረከቡ ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው በክኔሴት (የእስራዔል ፓርላማ) ንግግር እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
ከተለቀቁ ታጋቾች ቤተሰቦች ገሚሶቹን አግኝተው እንደሚያናግሩም ዘገባው አመላክቷል።
ከዚያም ወደ ግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ በማቅናት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመርን ጨምሮ 20 የሚሆኑ የዓለም መሪዎች በሚገኙበት የጋዛ የሰላም ጉባዔ ላይ እንደሚሳተፉ ቢቢሲ ዘገቧል።
በዮናስ በድሉ