Search

ሰንደቅ ዓላማችን በመላው ዓለም በድል የምንታወቅበት መለያችን ነው፡- ሜጀር ጄነራል ቡልቲ ታደሰ

ሰኞ ጥቅምት 03, 2018 57

ሰንደቅ ዓላማችን የኩራት እና የማንነታችን ዓርማ፣ በመላው ዓለም በድል የምንታወቅበት መለያችን ነው ሲሉ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ቡልቲ ታደሰ ገለጹ።
ሜጀር ጄነራል ቡልቲ ታደሰ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚከበርበት ልዩ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም እኛ ኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነታችንን ያረጋገጥነው በዚህ ሰንደቅ ዓላማ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ከቀለም የተሻገረ በመስዋዕትነት የከበረ ትርጓሜ እንዳለውም ገልጸው፤ ሰንደቅ ዓላማ ለመከላከያ ሠራዊት ያለው ትርጉም ጥልቅ መሆኑን ሜጀር ጄነራሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ደም እና ላቡን አፍሶ፤ አጥንቱን ከስክሶ መስዋዕትነት የከፈለ ነው ብለዋል፡፡
በቅኝ ግዛት የተገዙ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ ነፃነት ምሳሌ በመውሰድ፣ ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በመውሰድ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ማዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የሀገር ፍቅር ስሜት በሰንደቅ ዓላማ ይገለጻል ያሉት ሜጀር ጀነራል ቡልቲ፤ ለሀገር የተከፈ መስዋዕትነትንም ያሳያል ብለዋል፡፡
በሜሮን ንብረት