Search

ግብፅ ከጠብ አጫሪ መግለጫዎችና ኢ-ፍትሐዊ ከሆኑ የቅኝ ግዛት የይገባኛል ጥያቄዎች ልትቆጠብ ይገባል - የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

ሰኞ ጥቅምት 03, 2018 87

ግብፅ በዓባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬም ‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል’ ትርክቷን መቀጠሏን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው የግብፅ ጠብ አጫሪ አካሄድ መቀጠሉን አንስቶ፤ ሀገሪቱ ያወጣችው የቅርብ ጊዜ መገለጫ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ አለኝ በምትለው የተለመደ ታሪካዊ መብት የተቃኘ እንደሆነም ጠቁሟል።

የግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ፤ ከትብብር ይልቅ የኢትዮጵያን አቅም ዝቅ አድርጎ የመመልከት የከሸፈ እና የተሳሳተ ፖሊሲ እንድትከተል አድርጓል ሲል ጠቅሷል።

የታላቁ የዓባይ ወንዝ መነሻ እና 85 በመቶ የዓባይ ውኃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ግን በአንፃሩ የብልፅግና ጎዳና ላይ ነች ይላል መግለጫው።

ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በመጠቀም የመልማት ፍላጎቷን ለመገደብ የሚደረግ የትኛውም ጫና ከልማት ጉዞዋ አያስቆማትም ያለው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ ብልፅግና ምንም ዓይነት ትንኮሳ እና የእጅ አዙር ጦርነት ወደ ኋላ የማይመለሰው እንደሆነም አፅንኦት ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ እና ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ለአሥርተ ዓመታት በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሰረት የድንበር ተሻጋሪ ትብብርን እውን ለማድረግ ከግብፅ ጋር ለመስራት መሞከራቸውን የጠቀሰው መግለጫው፣ የትኛውም የትብብር ጥያቄ ግን በግብፅ የተሳሳተ አካሄድ ሲደናቀፍ መቆየቱን አስታውሷል።

መግለጫው አክሎም ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት፤ ዓመታዊ ሥራ ግምገማ እና በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ላይ፣ እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ በተደረገው የሦስትዮሽ ድርድር በቅን ልቦና ተወያይታ አታውቅም ብሏል።

ከዚህም ባለፈ ግብፅ የሌሎችን የተፋሰሱ ሀገራት ፍላጎትና መብት በመዘንጋት፤ የሙጥኝ ብላ ከያዘችው የቅኝ ግዛት ዘመን የመነጨ “ታሪካዊ መብት” አስተሳሰቧን ለመጫን ጥረቷን መቀጠሏንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቅሷል።

በተጨማሪም ግብፅ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ምንም ዓይነት ምክክር ሳታደርግ ከተፋሰሱ ውጭ ውኃ መቀልበስን ጨምሮ በርካታ ሕገወጥ እና ግዴለሽነት በተሞላባቸው ድርጊቶቿ የውኃ ብክነት ላይ ተሰማርታለችም ብሏል መግለጫው።

የዓባይ ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቀጥታ በመወያየት መሆኑንም የተነሳ ሲሆን፤ የውኃ ደኅንነት የሚረጋገጠው ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የዓባይን ወንዝ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲጠቀሙ ብቻ መሆኑንም ነው መግለጫው የጠቆመው።

የግብፅ እጣ ፈንታ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ፤ ብቸኛው ምክንያታዊ አማራጭ ግብፅ ከላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያላታን ግንኙነት ከዛቻ፣ ዘለፋ እና ሌሎች ያልተገቡ ድርጊቶች አፅድታ ከሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በእኩልነት ስትወያይ ብቻ ነውም ብሏል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ።

የግብፅ "ድርቅ ገጠመኝ" ስሞታ በፍጥነት ወደ "በጎርፍ ተጥለቅልቄያለሁ" ጽንፍ መቀየሩ ግብፅ የጋራ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ መፍትሄ የማግኘት መንገድ አለመፈለጓን ማሳያ እንደሆነ ያነሳው መግለጫው፤ ግብፅ ሱዳንንም ወደ ፈጠረችው ቀውስ ለመጎተት እየሞከረች ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድብ ላይ ውጤታማ ቅንጅት እንዳላቸውም የተጠቀሰ ሲሆን፤ ይህን ወንድማዊ ትስስራቸውን ወደ ሕዝባቸው የጋራ ልማት ማሸጋገር እንደሚቀጥሉም ነው የተገለፀው።

ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን የመገንባት እና የማንቀሳቀስ ልምድ ያላት ሀገር እንደመሆኗ፤ ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በግድቦቿ አስተዳደር ላይ በከፍተኛው የሙያ ብቃት እየሠራች ትገኛለችም ብሏል የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው።

ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ የደን ልማት ዘመቻ፤ የሕዳሴ ግድብን የሚጠብቅ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ እንደሆነ አንስቶ ግብፅ ከዚህ ልትማር ይገባል ብሏል።

መግለጫው በማጠቃለያው ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ላይ ካልተገቡ መግለጫዎችን እና ጠብ አጫሪ ድርጊቶች በመቆጠብ ለዲፕሎማሲያዊ መንገዶች እና የወዳጅነት አካሄዶች የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠቷን እንደምትቀጥል አጽንኦት ሰጥቷል።

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD