ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ያለን ስሜት እና ፍቅር የምንገልጽበት ምልክትም ነው፡፡
የአንድነት ተምሳሌት የሕብረ-ብሔራዊነት ማሳያ፤ ትንሽ፣ ትልቅ፣ ወጣት ሽማግሌ፣ ሳይለይ ሀገር በአንድ ቋንቋ የምትገለፅበት ሕዝቦችን በአንድ ስሜት ሚያስተሳስር ግዙፍ አርማ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ልጆች በትምህር ቤት የ‘ዜግነት ክብር’ እያሉ የሚዘምሩለት፣ ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ የሚያደርጉት፣ ወታደሮች በመስዋዕትነት የሚዋደቁለት፣ አባት እናቶች በጀግንነት ዘብ የቆሙለት የሀገር ክብር መገለጫ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የጀግንነት፣ የክብር እና የሀገር ፍቅር አንድ ላይ የሚገለፁበት አንድ ሆኖ በአርማው ውስጥ ሁሉንም የሚያሰባስብ እና አቅፎ የሚይዝ የሀገር ቀለም ነው፡፡
ለሰንደቅ ዓላማ የሚከፈል ዋጋ የሀገር ፍቅር ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማቸው ውድ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገርን በነጻነት ለትውልድ አስረክበዋል፤ ዛሬም ሰንደቃቸውን በክብር እየጠበቁ ነው፡፡
የዜግነት ክብር መገለጫ የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በመስዋዕትነት የደመቀ እና ኢትዮጵያውያን በየትም ዓለም በክብር ከፍ የሚያደርጉት የነጻነት ዓርማ ነው፡፡
በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ከምትገለፅባው ነገሮች መካከል ዋነኛው በልጆቿ ጀግንነት ተከብሮ ከፍ ብሎ የሚውለበለበው ሰንደቅ ዓላማዋ ነው፡፡
ልጆቿ ሰንደቅ አላማዋን ብለው በከፈሉላት መስዋዕትነት ነጻነቷን ጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ አፍሪካውያንም አርአያ በመሆኗ ሰንደቅ አላማው የፓን አፍሪካኒዝም እና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ሆኗል፡፡
ይህ ከመስዋዕትነት እና ከጀግንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጥቅምት በገባ በመጀመሪያው ሰኞ የሚከበር ሲሆን፣ ዕለቱ በጀግንነት ሀገርን ጠብቀው ላቆዩ ክብር የሚሰጥበት እና ሀገር ልዕልናዋን ጠብቃ ለትውልድ እንዲትተላለፍ ዜጎች ቃል የሚገቡበት ነው፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #ethiopianflag #flagday