ከዓመታት ስቃይ እና ደም መፋሰስ በኋላ የጋዛ ጦርነት አብቅቷል ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ፡፡
አሜሪካ፣ ቱርኪዬ፣ ግብፅ እና ኳታር በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው በግብፅ እየተካሄደ በሚገኘው የሻርም ኤል ሼክ የሰላም ጉባኤ ላይ ነው፡፡
ስምምነቱን የሀገራቱ መሪዎች የፈረሙ ሲሆን፤ ሰነዱ ቀጣዩን የጋዛ አስተዳድር በተመለከተ፣ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ እና በመልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱ በይፋ ከተፈረመ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ከዓመታት ስቃይ እና ደም መፋሰስ በኋላ የጋዛ ጦርነት አብቅቷል ብለዋል፡፡
ይህ ለውጥ እንዲመጣ ላደረጉ የአረብ እና የሙስሊም አገራትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አሁን በጋዛ የመልሶ ግንባታ ስራ ተጀምሯል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ ቀን እንዲመጣ በቀጠናው እና በአለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሲጥሩ፣ ሲመኙ እና ሲጸልዩ ነበር ብለዋል፡፡
ዛሬ የተፈረመው የጋዛ የተኩስ አቅም ስምምነት ሰነድ ታሪካዊ ነው ሲሉም መግለፃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሰላም ውይይቱ ላይ 20 የሚሆኑ የሀገራት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ የቱርክ፣ የፍልስጤም፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ኳታርና የሌሎች ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በአፎምያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #Gaza #peacedeal