Search

አፍሪካውያን ለምን የኢትዮጵያን ሰንደቅ በተለያየ መንገድ መጠቀምን መረጡ?

ሰኞ ጥቅምት 03, 2018 38

ከ20 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በራሳቸው ቅርፅ እና የራሳቸውን ምልክት በማኖር እንደሚጠቀሙበት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ተናግረዋል፡፡

ሀገራቱ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ላደረጉት የትግል ጉዞ የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያን እንደምሳሌ በመውሰዳቸው ሦስቱን ቀለማት እየቀያየሩ መጠቀም እንደጀመሩ ፕሮፌሰር አየለ ገልጸዋል፡፡

አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩን ቀለማት የሚጠቀሙት ቅኝ ግዛትን በማስወገድ ነጻነታቸውን የተጎናጸፉ አፍሪካውያን ብቻ እንዳልሆኑ የጠቆሙት ምሁሩ፣ በካረቢያን ደሴቶች የተመሰረቱ ሀገራትም ቀለማቱን የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ፣ የራሳቸው የነፃነት መለያ አርገው እንደሚጠቀሙት ተናግረዋል፡፡

ይህም ለኢትዮጵያ ድርብ ክብር እንደሆነ ነው ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ የጠቀሱት፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ኩራት በመሆኗ ሰንደቅ አላማዋን ሌሎች እንደ ነፃነት አርማ አድርገው እንዲጠቀሙበት የዓድዋ ድል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለማድረጉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ዛሬ ላይ ያለውን መልክ ከመያዙ በፊት ሦስቱ ቀለማት ለየብቻ የሚውለበለቡ እንደነበር አስታውሰው፣ እ.ኤ.አ በ1903 እንግሊዝ ሱዳንን ቅኝ ግዛቷ አድርጋ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው የድንበር ስምምነት ወቅት ሶስቱ ቀለማት በአንድ ተሳስረው የድንበር ወሰኑ ላይ መተከላቸውን አውስተዋል።

ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ እና ሌሎች ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነው ሰንደቅ አላማችን የሚከበርበትን ቀን ማሰባችን ለነፃነታችን የከፈልነውን መስዋዕትነት እንድናስብ የሚያደርግ ነው ሲሉም ተናግረዋል።   

በሔለን ተስፋዬ   

#EBC #ebcdotstream #EthiopianFlag #flag #nationalflagday