ቀድሞ እንደ ነውር ሲታይ የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከመሽኮርመም አልፎ በመሪዋ የአደባባይ ጥያቄ ከሆነ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡
የጠንካራ ባሕር ኃይል ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ከባሕሩ በቅርብ ርቀት ላይ ሆና ለባሕሩ ባይተዋር ከሆነች ከሦስት አሥርተ ዓመታት ባላይ አስቆጥራለች፡፡
ነገሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ ዜጎች እና ምሁራን የባሕር በር ጥያቄ ሲያነሱ እንደ ነውር ሲቆጠር የነበረ እና ጉዳዩን ያነሱ ዜጎች የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት እንደጣሱ ጭምር ሲቆጠር የነበረ መሆኑ ነው፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት በጉዳዩ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች አባላት ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግን የቀይ ባሕር ጥያቄ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተነጥላ መኖር እንደማትችል የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማግኘት የምትፈልገው ግን ትብብር ባስቀደመ ውይይት እንደሆነም ተናግረው ነበር፡፡
እነሆ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጀንዳውን አደባባይ ካወጡ በኋላ ጉዳዩ የዜጎች መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ የዓለም ማኅበረሰብም ጥያቄው ተገቢ መሆኑን አምኖበት ተቀብሎታል፡፡
የቀድሞ የባሕር ኃይል አባል የሆኑት ሌፍተናንት ሃለፎም መሰለ ከኢቲቪ 57 ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የባሕር በር ጥያቄው መነሳቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘግይቶ መነሳቱ እንደሚቆጫቸው ተናግረዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ስለሆነ የግድ መመለስ እንዳለበትም ነው የሚጠቅሱት፡፡
ጉዳዩ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ጉዳይ ስለሆነ ኢትዮጵያ ከባሕሩ ተለይታ መኖር አትችልም የሚሉት መኮንኑ፤ ጥያቄው ግን ሰጥቶ በመቀበል እና በትብብር መቀጠል እንዳለበት ነው ያነሱት፡፡
የኢትዮጵያ ጥያቄ በበጎ ታይቶ በንግግር መፍትሔ ካገኘ ባሕሩ ለሁሉም እንደሚበቃ ነው ሌፍተናንት ሃለፎም ያሳሰቡት።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #seaaccess #redsea #ethiopiannavy