ሀገራዊ ምክክሩ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሰጠና እምነት የተጣለበት መሆኑን በግልፅ አይተናል ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር የሆኑት ሂሩት ገብረሥላሴ ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በ11 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገራት እንደ ዋሽንግተን፣ ቶሮንቶ፣ ዱባይ ለንደን እና ስቶክሆልም ባሉ ከተሞች ውስጥ ውይይት ተደርጎ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መከናወኑንም ተናግረዋል።
በከተሞቹ ውስጥ አጀንዳ በተሳካ ሁኔታ መሰብሰቡን የገለፁት ዋና ኮሚሽነሯ፤ በቀጣይ በትልቁ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ተሳታፊዎች የሚወክሏቸውን ሰዎች መምረጣቸውንም ጠቁመዋል።
በውጭ ሀገራት ሲካሄድ የነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ይበል የሚያሰኝ እና አዎንታዊ ውይይት እንደነበርም ዋና ኮሚሽነሯ አውስተዋል።
በውጪ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲመኙት የነበሩትን ይህን ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልፀዋል።
በሴራን ታደሰ