የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለማስመለስ በርካታ የወደብ እና የባሕር በር አማራጮች እንዳሉ ልንገነዘብ ይገባል ሲሉ የሰላምና እርቅ እንዲሁም የውሃ ጉዳዮች ተመራማሪ እና አማካሪው ጋረደው አሰፋ ገለጹ።
የወደብ አማራጭ ስናስብ አንድ ብቻ ሳይሆን ዜይላ፣ በርበራ፣ አሰብ፣ አዱሊስ፣ ጅቡቲ እንዲሁም ምፅዋ ስለመኖራቸው ልንገነዘብ ይገባል ሲሉ አማካሪው ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
የባሕር በር አማራጭ ልየታ በምክንያታዊነት፣ አዋጭነት እና አስቻይ ሁኔታ ላይ ሊመረኮዝ እንደሚገባውም አንስተዋል።
እንዲሁም አማራጩን የሚሰጠው ሀገር ከኪራይ ባሻገር የሚያገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና መነቃቃት ማመላከት እንደሚገባ አክለዋል።
በዋቢነት ወደብ አልባ የሆነችው ኦስትሪያ የጀርመንን ሀምቡርግ ወደብ እንደምትጠቀም ገልጸው፤ ይህም ያለምንም ክፍያ መሆኑን ተናግረዋል።
በአፍሪካ ይህን መሰል የጋራ ተጠቃሚነት እስከአሁን እምብዛም ያልተለመደ በመሆኑ፤ ሰጥቶ የመቀበል መርህን መጠቀም የተሻለው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ኢትዮጵያ የሴራ ተጠቂ ናት” የሚሉት ተመራማሪው፤ ሀገሪቱ በሰሜን አቅጣጫ ከባሕር ያላት ርቀት 60 ኪሎ ሜትር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ከባሕር በር መራቅ ከተጠቃሚነት የማያግድ ስለመሆኑ አንስተው፤ ኢትዮጵያ በተጠና መልኩ ባለቤትነቷን እንድታጣ ስለመደረጓ በቁጭት ገልጸዋል።
“ከመቅረት ማርፈድ” በማለት ያነሳነው ጥያቄ በትክክልም መጻኢ ዕድላችንን ማቃናት የምንችልበት በመሆኑ አጠናክረን ልንገፋበት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ሂደት በቻልነው ልክ ያሉንን አማራጮች ሁሉ ልንጠቀም ይገባል ሲሉም አፅንዖት ሰጥተዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#ebcdotstream #ethiopia #redsea #seaport