በአንድ ንጉሥ ተጀምሮ፣ በዘጠኝ ሥርዎ መንግሥታት ተከናውኖ በ2 ሺህ 3 መቶ ዘመናት የተጠናቀቀው የትውልድ ቅብብሎሽ ፅናት ማሳያው ታላቁ ግንብ ሰው አልሠራውም እስኪባል ድረስ የምህንድስና ጥበቡ እና ዓላማው ዛሬም ዓለምን ያስደንቃል።
በእርግጥ ዛሬ ላይ ቻይና ከዓለም ሁለተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ ገንብታ በዓለም የልዕለ ኃያልነት መንበር ላይ መቀመጧን ለተመለከተ ስለዕድገቷ ምስጢር ብዙ ርቀት ሳይጓዝ የሚያያቸው ምክንያቶች እልፍ ናቸው።
ከብዙዎቹ ምክንያቶቹ አንዱ እና ዋናው የረጅም ጊዜ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ያለፈ የስልጣኔ እርሾ ያላት መሆኗ “እየደመሰሱ መቅዳት” የሚለውን መርህ በጥበብ ማለፏ ለዛሬ እድገቷ ምስጢር ዋናው መሆኑን መገመት የሚከብድ አይደለም።
ይህን ምስጢር ለማረጋገጥ ደግሞ በ2300 ዓመታት በዘጠኝ ሥርዎ መንግሥታት የመጣው መሪ ሁሉ አሻራውን አሳርፎበት የትውልድ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የቻይና ግንብ ዛሬም ሕያው ምስክር።
ታላቁ የቻይና ግንብ በወቅቱ ቻይናውያን ራሳቸውን ለመከላከል ያስፈልጋል ብለው ብዙ መክረውበት የጀመሩት በመሆኑ ነገሥታቱ ሁሉ ሲቀየሩ በአስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ስላልነበራቸው የሁሉም ዓላማ ግንቡን ማጠናቀቅ ላይ ሆኗል።
ግንባታው ሁለት ሺህ ዓመታትን የፈጀው እና በትውልዶች ፅናት ለውጤት የበቃው ታላቁ የቻይና ግንብ ከግንባታው ግዝፈት የተነሳ “ድራጎን” አግዟቸው ካልሆነ በቀር በሰው ልጅ አቅም ይህን መስራት አይቻልም እስኪባል ድረስ አስደናቂ ሆኗል።
የቻይና ግንብ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በነበረው ጊዜ ዓለም ሲሚንቶን አልፈጠረችም ቻይናም ይህን አታውቅም፤ እናም ቻይናውያን ይህንን ግንብ የገነቡት ከሩዝ ዱቄት እና ከኖራ ጋር ቀላቅለው በፈጠሩት እንደ ሲሚንቶ ያለ ውኃ የማያስገባ ማጣበቂያ በመጠቀም ነበር።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በነበረው በንጉሥ ቺን ሺ ሁዋንግ አማካኝነት ቻይናን ከሞንጎሊያውያን እና በአቅራቢያው ከሚገኙ ጠላቶቿ ለመከላከል እንዲያስችል በማለት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ሲጀመር በአንድ ትውልድ እና ዘመን እንደማይጠናቀቅ ይታወቅ ነበር።
ነገር ግን ቻይናን ከጠላት ለመከላከል አስፈላጊ ነው ተብሎ የታመነበትን ፕሮጀክት መሪዎቿ እና ሕዝቡ አንድነት ፈጥረውበት በመታመን ለፍጻሜ አብቅተውታል።
ዘመናዊ የምህንድስና መሳሪዎች ባልተፈጠሩበት ከዛሬ 2 ሺህ 700 ዓመታት በፊት የተገነባው የቻይና ግንብ የምድር ወገብን ግማሽ የሚያህል ማለትም ከ21 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት አለው።
እዚህ ላይ እንዲህ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት እንኳን መሥራቱ ገና ሃሳቡ የሚያደክም ቢሆንም ይህን የታሪክ፣ የአንድነት እና የጥንካሬ ነጻብራቅ የሆነውን ፕሮጀክት ጀምሮ ማጠናቀቅ ከስኬትም በላይ ነው።
ይህን የሚያክል ግዙፍ ግንባታ ሲከናወን እንደየአካባቢው ሁኔታ የግንባታ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ጭምር የተገነባ መሆኑ ደግሞ ሌላው የተለየው የስኬት ምንጩ ነው።
በወቅቱ የግንባታው ቦታ ረጅም እና መልክዓ ምድራዊ ልዩነቱ ሰፊ ስለነበር የግንባታ ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ እጅግ ፈታኝ ሥራ ነበር። ቻይናውያን ለዚህም ሥራ መፍትሔ የሰጡት የሀገር በቀል ዕውቀትን በመጠቀም እና በየአካባቢው ያለ ሃብትን ለግንባታው በማዋል ነበር።
በዚህም መሰረት ድንጋይ እንደልብ በሚገኝባቸው ቦታዎች ድንጋይ በመጥረብ እና በማስተካከል ለማጣበቂያነት ደግሞ የሩዝ ዱቄት እና ኖራ በመቀላቀል ባዘጋጁት ሲሚንቶ መሰል ቁስ ግንባታውን ያከናውኑ ነበር።
በአካባቢው የሚገኙትን እንደ እንጨት፣ የተለያዩ እፅዋት፣ አፈር እና ድንጋይ በመጠቀም አልፎ አለፎ ደግሞ ድንጋይ በሌለባቸው አካባቢዎች ከጭቃ የተሠራ ጡብ በመጠቀም ነው ግዙፉን ፕሮጀክት ያከናወኑት።
ዋና ዓላማው ቻይናን ከጠላት መከላከል የነበረ ቢሆንም ቀጣይ ትውልድ በሰላም ይኖር ዘንድ ባላቸው ጠንካራ ጉጉት የግንባታ ሥራውን በጥራት ማከናውን ቁልፍ ጉዳይ አድርገው ነበር። በግንባታው ወቅት የሥራው ጥራት በሚገባ ከተፈተሸ በኋላ የተቆጣጣሪው ስም በየግንቦቹ ክፍሎች ላይ ተቀርፆ ይለጠፍ ነበረ፡፡ ይህም ሥራው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እና ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ በኩል በዘመኑ የነበረውን የጥራት ማስጠበቂያ ዘዴን ከመንገር አልፎ ዛሬም ትምህርት የሚወሰድበት ሆኗል። ለትውልድ በሚተላለፍ ፕሮጀክት ውስጥ ስሙን ማን በመጥፎ ማስቀመጥ ይፈልጋል? ይህ የጥራት ቁጥጥር ሥራቸው እና ዘዴው ዛሬም ቢሆን አስተማሪ ነው።
ግንባታው ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ከሰው ባለፈ ተፈጥሮንም ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ሌለው አስገራሚ ጉዳይ ነው። ምስጥን የመሰሉ ጎጂ ነፍሳት በተለይ በእንጨት እና የአፈር ጡበ የተሠራበትን አካባቢ እንዳይጎዳ ተፈጥሯዊ መከላከያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል።
አንድ ዓላማ ባስተሳሠራቸው ትውልዶች ለሺህ ዘመናት በፈጀ ድካም እና ጥንካሬ ለውጤት የበቃው ይህ ግንብ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በአፈ ታሪክ በቻይናውያን ዘንድ ተወዳጅና መንፈሳዊ ትርጉም ባለው ድራጎን ታግዘው እንጂ በሰው ዕውቀት እና ጉልበት አልተሠራም እስኪባል ድረስ የሰው ልጆች የግንባታ ጥበብ የሚታይበት ሥራ ሊሆን በቅቷል።
ያልታደሉ ሀገራት ለትውልድ ዕዳ እንደሚያስተላለፉ ሁሉ አንዳንድ ሀገራት በረከት የሚሆን ሥራ በማውረስ የሀገር መሰረት ፅኑ እንዲሆን አድርገዋል። ቻይና ብዙ የሀገር ማፅኛ መሰረቶችን ለትውልድ በማስተላለፍ ምሳሌ መሆኗ የሚካድ ባይሆንም ለትውልድ የሚሆን የመግባቢያ ፕሮጀክት በማስተላለፍ ግን ለሌሎች ሀገራትም ተምሳሌት ነች።
ዛሬ ላይ ቻይናውያን በቀድሞ አያቶቻቸው ዘመን እንዴት ሀገርን ከጠላት ለመከላከል እንደቻሉ የሚማሩበት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ የሰሩበት ጥበብ፣ የሀገር መሥሪያ መሰረቱን ያጸኑበት ዘዴ፣ የሀገር ዓላማ የተሳካበት የተለያየ የመንግሥት ዘመን፣ ሀገርን ያስቀደሙበት ሕብረትን በዘመናዊት የቻይና እድገት ውስጥ ተምረውበታል ደግሞም ሰርተውበታል።
ዛሬ ላይ ከቻይና እና ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች በሚመጡ በዓመት ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚጎበኘው ይህ ታላቅ ግንብ የቻይናውያን የጥንካሬ እና አንድነት ማሳያ ነው። ዛሬም ቻይናውያን ይህን ምሰሶ እየጎበኙ ፅናትን፣ ሀገር መውደድን እና ቻይናዊንትን እያደሱ በሕይወታቸው ይመነዝሩታል።
በብዙ ዘመናት ተከናውኖ በአንድ ዘመን ደግሞ ተጠናቆ ዛሬ ላይ የደረሰው ታላቁ የቻይና ግንብ ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል በተከታታይ በመጡ ሥርወ መንግሥታት በቅብብሎሽ ተከናውኗል።
እናም ዛሬ ቻይና ይህን ግንብ ጠላትን ለመከላከል የተገነባ ነው ብላ ብቻ አታልፈውም። ይልቁንም የፅናት እና የዘመናዊት ቻይና መሰረት በማድርገ መስፈንጠሪያ ታሪኮቿ መካከል አንዱ ሆኗል።
በዓለም ታሪክ ውስጥ ገዝፎ የሚታይ የረጅም ጊዜ ራዕይ የላቀ የምህንድስና ጥበብ እና የትውልድ ቅብብሎሽ ተምሳሌት የሆነ የጋራ ዓላማና ፅናት ውጤት ነው።
እንዲህ ያለ ወረትን ለትውልድ የሚያስተላልፉ ሀገራት በእርግጥም ሀገር ከማፅናት ባለፈ መጪው ትውልድ ከችግር የሚወጣበትን መንገድ ማመላከታቸው አይቀርም።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ስለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲናገሩ “ሕዳሴን ከማጠናቀቅ ይልቅ አለማጠናቀቅ ቀላሉ መንገድ ነው። ግን ጥርሳችንን ነክሰን መክፈል ያለብንን ሁሉ ከፍለን ለቀጣዩ ትውልድ የሰንደቅ ከፍታ ማሳያ የሚሆን የይቻላል እና የፅናት ውርስ ማስተላለፍ አለብን።” በማለት የተናገሩት።
እርግጥ ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደቻይናው ግንብ ሁሉ አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። ይልቁንም የመጪው ዘመን የፅናት ምልክት ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ ያለፈችበት ረጅም ዘመን “እየደመሰሱ መቅዳት” ቢበዛበትም በሕዳሴ ግድብ መመረቅ ማከም ተጀምሯል። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ለትውልድ የሚሻገሩ ተቋማትን መፍጠር እና ማስቀጠል እንደሚችሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሕያው ምስክር ሆኖ ዛሬም አለ።
እናም ልክ የዓድዋ ድል ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የነጻነት ፋና እንደሆነ ሁሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብም ለነገው ትውልድ የሀገር ብልጽግና ማጽኛ መሰረት የጣለ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
ዋሲሁን ተስፋዬ