Search

ጥቂት ሀገራት ብቻ የሚያሳኩትን ደረጃ ኢትዮጵያ እንዴት አሳካችው?

ዓርብ ጥቅምት 07, 2018 11828

ኢትዮጵያ በመድኃኒት ቁጥጥር አቅም የዓለም ጤና ድርጅት ደረጃ ሦስትን (ML3) ማግኘቷ ተከትሎ የጤና ሚንስትር / መቅደስ ዳባ ጉዳዩን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ይህ ስኬት ኢትዮጵያ መድኃኒቶችን የመቆጣጠር እና የሕዝብ ጤናን የመጠበቅ አቅሟ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት ይህ ዕድገት ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሻሻል፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ጥራት ያለው መድኃኒት እና የሕክምና ምርቶችን ለማቅረብ ብቁ መሆኗን ማሳያ ነው፡፡

ለመሆኑ ደረጃ ሦስት የመድኃኒት ቁጥጥር (ML3) ምንድን ነው?

በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ‘ግሎባል ቤንችማርኪንግ መሳሪያ (GBT)’ መስፈርት መሰረት ደረጃ ሦስት የመድኃኒት ቁጥጥር (ML3) እንደ መድኃኒት፣ ክትባቶች እና የሕክምና መሣሪያ ምርቶችን መቆጣጠር የሚያስችል የተረጋጋ፣ በጥሩ ሁኔታ የሚሠራ እና የተቀናጀ ሥርዓትን መዘርጋቱን ያመለክታል።

የአንድ ሀገር የጤና ሥርዓት ያልተደራጀ ምላሽ ሰጪ ሥርዓት ከሆነው ደረጃ ሁለት (ML2) መደበኛ ሂደቶችን ወደሚከተለው፣ አንዲሁም ዓለም አቀፍ አሰላለፍ ውስጥ ተለይቶ ወደሚታወቀው ደረጃ ሦስት ለመሸጋገር በርካታ ሊታለፉ የማይችሉ መስፈርቶችን ማሟላት አለበት።

የግብይት ፈቃድ፣ ክሊኒካዊ ሙከራዎች፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ሥርጭትን ጨምሮ ለሁሉም ዋና ዋና የቁጥጥር ተግባራት ግልጽ እና አጠቃላይ ሕጎች እና መመሪያዎችን ማዘጋጀት የመጀመሪያው መስፈርት ነው።

እንደ የምርት ፈቃድ፣ የገበያ ክትትል እና ቁጥጥር፣ የደኅንነት ክትትል፣ ምርመራ እና ፈቃድ አሰጣጥ ያሉ ውጤታማ የቁጥጥር ተግባራት ያሉ ሕጎች እና መመሪያዎች ተግባራዊ መሆናቸውን መከታተያ ስልት ደግሞ ሌላው መስፈርት ነው፡፡

ወጥ የሆነ የአፈጻጸም እና ቀጣይነት ያለው መሻሻልን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የጥራት አስተዳደር ሥርዓት (QMS) መዘርጋት ሌላው ወሳኝ መስፈርት ነው።

ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ተልእኮውን በዘላቂነት ለመፈፀም በቂ የገንዘብ ድጋፍ፣ የሰለጠኑ ሠራተኞች (ባለሙያዎች) እና አስፈላጊ መሣሪያዎችን ማሟላት አለበት፡፡

በተለይም ዲጂታል የቁጥጥር መሣሪያዎች ወቅታዊ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለማቅረብ ወሳኝ በመሆናቸው እንደ መሰረታዊ መስፈርት ይታያሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ግሎባል ቤንችማርኪንግ መሣሪያዎችን (GBT)’ መስፈርቶችን ተከትሎ ከላይ የተጠቀሱ መስፈርቶችን ያሟላን ሀገርን ስልታዊ መንገድን በመከተል ለደረጃ ሦስት(ML3) በእጩነት ይመርጣል።

ሀገሪቱ ያለችበትን አፈጻጸም ለመገምገም እና በሁሉም የቁጥጥር ተግባራት ላይ ክፍተቶች ካሉ ለመለየት የዓለም ጤና ድርጅትግሎባል ቤንችማርኪንግ መሣሪያዎችን(GBT)’ መመዘኛዎችን በመጠቀም ግምገማ እንዲያካሄድ ፈቃደኛ መሆን አለባት።

የሀገሪቱ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በሕጋዊ ማዕቀፎች፣ በድርጅታዊ መዋቅር፣ በበሥራ ሂደቶች እና በሀብቶች ቁጥጥር ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለመፍታት ግልጽ የድርጊት መርሐ-ግብሮችን እና የጊዜ ሰሌዳዎችን የያዘ ስልታዊ ዕቅድ (IDP) ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።

እንደ የሕግ ማሻሻያ፣ የአቅም ግንባታ፣ የትግበራ ሥርዓት፣ዲጂታላይዜሽንእና ዘላቂ የገንዘብ ድጋፍ ያሉ ዋና ዋና ተግባራት መጠናከራቸው ሌላው በዓለም ጤና ድርጅት የሚገመገም ጉዳይ ነው፡፡

መስፈርቶቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጋቸውን እንዲሁም ቀጣይ እና አስተማማኝ ውጤቶችን እንደሚያስገኙ መረጋገጥ አለበት።

ኢትዮጵያም በዚህ ሂደት ውስጥ አልፋ መስፈርቶቹን በብቃት በማሟላቷ ነው የዓለም ጤና ድርጅት መድኃኒት ቁጥጥር ደረጃ ሦስት (ML3) የተሰጣት፡፡

ስኬቱ ኢትዮጵያ ለሕዝብ ደኅንነታቸው የተጠበቀ፣ ውጤታማ እና ጥራት ያላቸው መድኃኒቶች ለተጠቃሚዎች መቅረባቸውን ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ / መቅደስ ዳባ ተናግረዋል፡፡ ለመጨረሻው ደረጃ አራት (ML4) አቅም እንደሚሆንም ነው የጠቆሙት።

ደረጃውን የሚሰጠው የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ኢትዮጵያ ደረጃ ሦስት(ML3) በማሳካቷ በአፍሪካ ደረጃውን ያሳኩ እንደ ግብፅ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ዝምባብዌ፣ ሴኔጋል እና ሩዋንዳ ያሉ ጥቂት ሀገራትን መቀላቀሏል አብስሯል፡፡

የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ML3’ የደረሱ ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ 16 ብቻ ሲሆኑ፣ ደረጃ አራት (ML4) የደረሱ ሀገራት ደግሞ ደቡብ ኮሪያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ሲንጋፖር ብቻ ናቸው፡፡

ዕውቅናው ሕዝባዊ አመኔታን የሚያጠናክር፣ ለዓለም አቀፍ ትብብር በር የሚከፍት እና የኢትዮጵያን የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል የመሆን ራዕይን የሚደግፍ እንደሆነ ነው የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ የገለጹት፡፡

ደረጃው የኢትዮጵያ መንግሥት የቁጥጥር አቅምን ለማሻሻል እና ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ውጤታማ እና ጥራት ያላቸውን የሕክምና ምርቶች ለሁሉም ሕብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ተጠቅሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት በገጹ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ስኬት ከብሔራዊ የስኬትነት አልፎ የቀጣናው ስኬት ጭምር እንደሆነ አመላክቷል፡፡

ስኬቷ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የወደፊት የጤና ምርቶች ደንብን መቅረጽ እንደምትችል እና ደኅንታቸው የተጠበቀ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የሕክምና ምርቶችን ለእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ተደራሽ ማድረግ እንደምትችል እንደሚያሳይም ድርጅቱ ጠቁሟል።

 

በለሚ ታደሰ