Search

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የሕይወት ታሪክ

ሰኞ ጥቅምት 10, 2018 12068

ኢንና ሊላሂ ወኢንና ኢለይሂ ራጂዑን

ሁላችንም የአላህ አገልጋይ ነን። ወደርሱም ተመላሾች ነን።

በላቀ ምግባር፣ በጠለቀ ተግባር፣ በታመቀ ፍቅር፣ በእንግልት ማኅደር፣ በትግል መዘውር፣ የገዛ ነፍሥን በቁም ነጥቆ ለቸሩ ፈጣሪ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሐገር መሰዋዕት አድርጎ መባጀትም መዋጀትም የጥቂቶች የልዕልና እና የቅድስና መሰፈሪያ ነው።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የዚህ ውካይ፣ ከዚያም በላይ የሐገር ቀለምና ልክ፣ የዘመናት መልክ፣ አድባረ ታሪክ፣ የትውልዶች ድልድይ፣ የዕውቀትና የመልካም ጠባይ ሙዳይ፣ የደጋግ ሸሆች ብቃይ እና ቅጣይ፣ ሰብዓዊ ጠሐይ፣ በሁለንተና ሁሉን ዜጋ አገልጋይ፣ የሐገር ጥንታዊ ጥሪት፣ የሚጨበጥ ትውፊት፣ የሚዳሰስ ሐገረ-ሰባዊ ድባብና ቅርስ፣ ብጤ አልባ ሰብዓዊ ሐብት፣ ብርቅዬ የወል ሕያው ወረት፣ አንጡራ ሊቀ ሊቃውንት፣ ኅብር የሃይማኖት የብሔር እና የፖለቲካ አስተሳሰብ የማይቃረናቸው የሐገር እናት የዜጎችም መጠለያ ማሕፀን ነበሩ።

እኚህ ድንቅ የዘመን ቡራኬ ስብዕና በአጋጠማቸው ህመም ምክንያት ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በዘጠና ዐራት ዓመታቸው ጥቅምት 10 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከአባታቸው አቶ ኢድሪስ ዘለቀ እና ከእናታቸው / መነን ሽፋው 1924 ዓ.ም በወሎ ቦረና ገነቴ አካባቢ ልዩ ስሙዳሎታበተባለ መንደር ተወለዱ። ለአባትና ለእናታቸው ዐራተኛ ልጅ ነበሩ። እናትና አያታቸውን በልጅነት ተነጥቀው ነው ያደጉት።

በዕድገታቸው ወቅት የመንፈሳቸው ምሪት በቤተሰብ ስስትና ሥነ-ልቡናዊ ቅኝት ቢታጠርም፣ ወሰኑን ሰብረው እስከ ኅልፈት ለተንጸባረቁበት የሕይወት ዳና እራሳቸውን ሰጡ። ከምቾት አፀድ ወጥተው ከሥጋ ድካም ጋር የሚፀድቁበትን ዕጣ ፈንታ ገለጡ። እረኛም፣ ገበሬም፣ ነጋዴም ለመኾን የሞከረው ልጅነታቸው መጽደቂያ ፍኖቱ ግን - ዕውቀት ትምህርት እና ሥርዓት የነገሠበት አምባ ነበር። ይህም በብዙ ፈርጅ የሚገለጥ፣ የሚበየን፣ የሚሰነድ ቡቃያ አለው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመርገነቴ ዳሎታከሸህ ከማል እሸቴ የቅዱስ ቁርኣን ከፊል ነቢብ ተማሩ።ለገሂዳከሸህ አሊ ገመች የቅዱስ ቁርኣን ነቢብ፣ የዓቂዳ (ሥነ መለኮት) ትምህርት ገበዩ። ወደ ዳሎታ ተመልሰው ከሸህ ከማል የሐነፊ ፊቕህ (ሥነ ሕግ) አገባደዱ።ጥላንታወደ ሸህ አሊ አደም አቅንተው ቀሪ የፊቕህ ዕውቀት ሰነቁ። ወደ ዳሎታ ተመልሰው ከሸህ ዩሱፍ ተሰማ የፊቕህ (ሥነ ሕግ) ዝግጅት አጠናቀቁ።

በመቀጠል ወደቦረና ውሻትሄደው በሸህ ጡሓ በጌምድሬ አማካኝነት የነሕው (የሰዋሰው) ትምህርት ጀመሩ። ወደከቶአምርተው በዐቢይ የዘርፉ መምህራቸው በሸህ ዐብዲል ሐሚድ በሽር አጠናቀቁ። ጉዟቸውን ሳያናጥቡ ወደቦሩባ ገዳበሸህ የሕያ ሰዒድ አማካኝነት የቅዱስ ቁርኣን ተፍሢር (አንድምታ) ገበዩ። በመጨረሻም በደሴ እና በአዲስ አበባ ከተማዎች ከሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ዘንድ የሐዲስ፣ የመንጢቅ፣ የበላጋ፣ የዓሩድ፣ የበዲዕ፣ የእስቲዓራ፣ የመዓኒ፣ የሒከም የትምህርት ዘርፎችን ቀሰሙ።

በዚህ ሂደት አዕምሯቸውን እና ልቡናቸውን ከአለመለሙ በኋላ መንፈሣዊ ቁመናቸውን ወደ ማነጽ ተሸጋገሩ።

ከሸህ ሐሰን ፈቃዱ የተለያዩ ዕለታዊ ዊርድ (መዘክር) አገኙ። እንደ አብራሔ በሚቆጥሯቸው እና በዘጠነኛው የኢትዮጵያ ዓሊሞች (ሊቀ ሊቃውንት) የበላይ ጠባቂ በሣልሣዊ  ዳንይ (ሸህ ሙሐመድ ዘይን) በኩልም የአዝካር የኸልዋ ጽሞና እና ተመስጥኦ ሙሉ ፈቃድ ወረሱ። 'ሸህ አሕመድ ኑር (አበል ጀማል) ጅማ' አማካኝነት ቋሚ ተጨማሪ የዚክር ወረት የማካተት ዕድል አገኙ። በሸህ ሙሐመድ ኮሬብ እንዲሁም በየመናዊው በሸህ ሰይድ አሕመድ ዓሊ የመኒ አማካኝነት መንፈሣዊና መለኮታዊ ቅዱስ ንባቦችን ለመከወን የሚያስችል ችሮታም አገኙ።

ይህም ሂደት በዐስራ ሦስት መምህራን ድጋፍ በሰላሳ ዐምስት ተከታታይ ዓመታትና የሙሉ ጊዜ ጥረት ተጠናቀቀ።

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ  መምህር (ሙደሪስ ሙዓሊም)” የኾኑት ገና በተማሪነታቸው (በደረስነታቸው) ወቅት ነው፡፡ ምንም እንኳን ምቾትና ተድላ ያልነበረ ቢኾንም የእረፍት፣ የቤተሰብ ዚያራ፣ የግል የትምህርት ክትትል ትኩረታቸውን ቀንሰው ለእኩዮቻቸውና ለበታቾቻቸው ያወቁትን ያካፍሉ ነበር፡፡ በዳሎታ፣ በጥላንታ፣ በከቶ የዕውቀት ማዕከላት የከፍተኛ ደረሳ ማዕረግ አግኝተው በርካታ ዓሊሞችን ማስተማር ችለዋል፡፡

በዕውቀት መምህሮቻቸው ተገምግመው ተመጣጣኝ የመምህርነት ቁመና ሲያገኙም 1958 1959 1960 ከሦስት መምህሮቻቸውየመምህርነት ፈቃድ (ኢጃዛ)” አገኙ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 1960 ጀምሮ እስከ መስከረም 2018 ድረስ - በአንዋር እና በኑር መስጅዶች፣ በበኬ እና በሰፈራ አካባቢ ባቋቋሟቸው የዕውቀት ማዕከላት እልፍ አዕላፍ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የሚጎርፉ ዕውቀት ፈላጊዎችን ያስተምሩ፣ ለመምህርነት አብቅተውም ያሰማሩ ነበር፡፡

ይህንን ሲያደርጉ ከየትኛውም አካል ደመወዝ ሳይጠይቁ፣ በተለይም ኑሯቸውን ማደላደል ከቻሉበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ የደረሳዎችን መሠረታዊ ፍላጎት እራሳቸው እያሟሉ ያገለግሉ እና ትውልድን ያለሙ ነበር፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የዕውቀት፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በመመስረት ሂደት የላቀ ተሳትፎ አላቸው፡፡ በዐስራ አምስት ዓመታቸው አንድ መስጅድ፣ አንድ ኸልዋ፣ አንድ የሸኻቸውን የመኖሪያ ቤት ብቻቸውን በግል ጉልበትና ግብዓት መመስረት ችለዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ እስከ ኅልፈታቸው ወቅት በአዲስአበባ ዘጠኝ መስጅዶችን፣ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል በመቶዎች  የሚቆጠሩ በርካታ የዕውቀትና የአምልኮ ተቋማትን በቀጥታና በሙሉ ድጋፍ እንዲሁም በማስተባበር መስርተዋል፡፡

1967 የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጠቅላይ ምክር ቤት ሲቋቋም ከቀዳሚ አባላት መካከል በመኾን በተቋም ግምባታው ሂደት እስከ 2014 ድረስ ደማቅ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡ ለተቋሙ ሕጋዊ ተክለ-ሰውነት በማጎናጸፍ ጥረት ውስጥም የጎላ ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ የኢስላማዊ ባንክ፣ ሚዲያዎች፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲመሠረቱና እንዲስፋፉ በማበረታታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በደረሳነታቸው ወቅት  በተለያዩ የዕውቀት ማዕከላት ለረዥም ጊዜያትአሞጣይ” (አስጠኝ) ኾነው ደረሳዎችንና የዕውቀት ማዕከላትን መርተዋል፡፡ አስተዳድረዋል፡፡ 1959 ወደ አዲስአበባ ከአቀኑበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ፤

·       1960 ጀምሮ በኑር መስጅድ 16 ዓመታት በምክትልነት እና 3 ዓመታት በዋና ኢማምነት

·       1967 የቀዳሚው የእስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት መስራች አባል

·       የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች ጉባኤ ሰብሳቢ

·       የቀዳሚው የኢትዮጵያ ዓሊሞች የፈትዋ ኮሚቴ መስራችና አባል

·       የሐገር አቀፍ የዑለማ ጉባኤ ሰብሳቢና ሙፍቲ የነበሩ ሲኾን በዚሁ ወቅት በዐስራ አንድ ዓመታት ውስጥ 58 የኢትዮጵያ ከተማዎች ተዟዙረው በሙስሊሞችና በሙስሊሞች እንዲሁም

      በሙስሊሞችና በሌሎች ወገኖች መካከል 130 በላይ ለቅራኔና ለግጭት የጋበዙ አጀንዳዎችን እልባት መስጠት ችለዋል፡፡

·       የአዲስአበባ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና ለዘጠኝ ዓመታት ዋና ሰብሳቢ

·       የኢፌዴሪ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጂ እና ዑምራ ዘርፍ እንዲሁም የዳዕዋና የትምህርት ዘርፍ ተጠሪ

·       2010 በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ

·       2011-2014 የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዝደንት

·       1960-2018 ድረስ በተለያዩ መስጅዶች በመምህርነት፣ በስነ ምግባር እነፃ፣ በመካሪነት አገልግለዋል፡፡

በሌላ በኩል በብሔራዊ የሰላም፣ የዕርቅ፣ የሽምግልና፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች እና ቡድኖች አባል እና አስተባባሪ በመኾን ያገለገሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር በደረሳነት ዘመናቸው በድምሩ 370 በላይ ድርሳናትን በእጃቸው ገልብጠው(Copy አድርገው) ጽፈዋል፡፡ ከሰማኒያ በላይ የዓረብኛ እና የዓጀም የግጥም መድብሎችን አዘጋጅተዋል፡፡ እንዲሁም ለሕትመት ያልበቁ፦ የኢትዮጵያ ዓሊሞች ዝክረ ታሪክ (በዓረብኛ) የእራሳቸው ግለ ታሪክ (በዓረብኛ) ሰባት የአማርኛ ትርጉም መጻሕፍትን፣ የቅዱስ ቁርኣን የአማርኛ ሰፊ ማብራሪያና ትንታኔ አዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የቅዱስ ቁርኣን ትንታኔን ጨምሮ ሌሎች የእነጻ መሰናዶዎች 360 በሚበልጡ ሲዲዎች እንዲሰነድ አስችለዋል፡፡

ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንደ ገለልተኛ ጸሐይ አንጸባራቂ የሕይወት መርሆች ነበሯቸው፡፡  ሠውነት ይቀድማልፈጣሪን አናሞኘው የልባችንን ይመለከታል  እንስሳ አምሳያውን በማይጎዳበት ሥነ ተፈጥሮ ሠው ሠውን እንዴት ይጎዳል?”  የሐገር ችግር በጥሩ መሪ በጥሩ ተመሪ ይቀረፋል  ሠውን የሚጠቅመው ወይም የሚጎዳው ዘሩ ሳይኾን ስራው ነው!”አንድነት ይበጃል መተባበር ይጠቅማል!”ሳይርበን አንበላም! ስንበላም እስክንጠግብ አንመገብም!” ...የሚሉ እና በቀላሉ ዕዝነ ሕሊናን ዘልቀው፣ ሰርነ ልቡናን ጥሰው የሚቆጣጠሩ የሕይዎት መርህ ነበራቸው፡፡ ሰርቶ በማብላት፣ ጠንክሮ በመስራት፣ አግኝቶ በማካፈል፣ ለሌሎች በመኖር ተግባራቸውም ሕያው ተምሳሌት ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ከአንደበታቸው ሳይዘነጉ፣ ከዱዓቸው ሳያጎድሉ፣ የእንባ ዘለላቸውን ሳይከትሩ ለሐገር ታምነው፣ በሐገር ፍቅር ተሸምነው ኑረዋል፡፡ በዓድዋ የተሰው አጎታቸውን አርበኛ ፋርስ ቱፋን በክብር ኩራት ከማመስገን ጀምሮ፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጻዊያን አቻ ሊቀ ሊቃውንት ጋር በአደባባይ እስከመሟገት የሚወሳ ተጨባጭ በረከት አላቸው፡፡

በአስቸጋሪ ወቅቶች ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚበጅ አቅጣጫ በመስጠት፣ መንፈሣዊ ግሳጼ እና ለበጎ ስራ ቡራኬ በመለገስ ለሐገር ሽግግር እንዲሁም መረጋጋት ንጹህ ድርሻ አላቸው። ለሐገር ልማት፣ ለውጥ እና ዕድገት ሁለንተናቸውን ተባባሪ የማድረጋቸውም ምስጢር የሐገር ፍቅር ነው።

ከዐስራ ሁለት በሚበልጡ የመካከለኛው ምስራቅና የምዕራቡ ዓለም ሐገራት በተዟዟሩበት ወቅትም ሐገራቸውንና ባሕላቸውን የሚያፈነጥቅ መልዕክትና አለባበስ ከማቅረብም ተቆጥበው አያውቁም ነበር፡፡ አዲሱ ትውልድ ሐገሩን እንዲወድ፣ ሁሉም ዜጋ ለሐገሩ እንዲተባበር ከመምከር የታቀቡበት ጊዜ አልነበረም።

በቀደምት ሊቀ ሊቃውንት ከፍተኛ ማዕረግና ምስክርነት ያገኙት፣ ለዐስርት ዓመታት ባበረከቱት ነጻ ሁለንተናዊ ግልጋሎት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲሁም ሃይማኖተኛ ዘንድ አንጸባራቂ ልባዊ ምስጋና የተጎናጸፉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ - 1966 በመሠረቱት ትዳር ዘጠኝ ልጆችን ያፈሩ ሲኾን፣ እልፍ አዕላፍ ዓሊሞችንና ደረሳዎችን እንዲሁም የዕውቀት ማዕከላትን መተካት ችለዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር  ኢድሪስ በእግራቸው ተጉዘው ያከናወኑትን ጨምሮ አርባ ጊዜ የሐጂ ሥነ ስርዓት አከናውነዋል፡፡ እስከ መስከረም 2018 ድረስ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ ንቃታቸው እጅግም የተሟላ ነበር፡፡

ከሳምንቶች በፊት በአጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም ምክንያት የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ዕለተ ዕሁድ ጥቅምት 10 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም አርፈዋል፡፡ አላህ የጀነት ያድርጋቸው።

ምንጭ፦ ከሕይወት ታሪካቸው