የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ግዴታውን በጽናት የሚወጣው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በረጅም ታሪኩ ያላሸነፈው ጦርነትና ያልተወጣው ሀገራዊ አደራ የሌለው የድል አድራጊነት ምልክት ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችን ታሪካዊ ጀግንነት በውጭ ወራሪዎች ላይ በተቀዳጃቸው ታላላቅ ድሎች ብቻ ሳይሆን የሀገርን አንድነትና ሕልውና ለማስቀጠል በከፈለው ወደር የለሽ መስዋዕትነቱ ጭምር የተረጋገጠ ነው።
ይህን ታሪካዊ የድል ሠራዊት ወደ ላቀ የውጊያና የስትራቴጂያዊ ዝግጁነት ደረጃ ለማሸጋገር በመደመር መንግሥት የተወሰዱት የሪፎርም እርምጃዎች ተቋሙን ከባህላዊ አደረጃጀትና አሠራር አላቅቀው ወደ ዘመናዊ እና አስተማማኝ የሀገር መከታነት ቀይረውታል።
ሪፎርሙ የመከላከያ ተቋሙን ገለልተኝነት፣ ሙያዊ ብቃት፣ የትዕዛዝ መስመር ጥንካሬ እና የተቋማዊ ስብዕና ግንባታን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ፤ ሠራዊቱ ማንኛውንም ሀገራዊ ጥሪ በከፍተኛ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚመልስበት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
በቴክኖሎጂና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ አቅም ግንባታ በኩል የተከናወነው ሪፎርም፣ የሠራዊቱን የመከላከልና የማጥቃት አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ሠራዊቱ አሁን ባለው ቁመና ዘመናዊ የስለላ፣ የድሮን፣ የሳይበር ደህንነት፣ የተቀናጀ የመሬትና የአየር ውጊያ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ በመሆኑ፤ የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ የመቀልበስና የመቆጣጠር ስትራቴጂያዊ የበላይነትን ተቀዳጅቷል።
የድል ሠራዊትነቱንና የቴክኖሎጂ አቅሙን በተቋማዊ መልኩ አጠናክሮ ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉ የሥልጠና እና የሰው ኃይል ልማት ሥራዎች የሠራዊቱን የውጊያ ዝግጁነት በየጊዜው የሚያድሱ አንቀሳቃሽ ሞተር ሆነዋል።
ዘመናዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ከታሪካዊው ወታደራዊ ጀግንነት ጋር ያቀናጁ የላቁ ማሰልጠኛ ተቋማትና አካዳሚዎች ተስፋፍተው በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ በመሆናቸው፤ የነገዋን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚችል የሰለጠነና ዕውቀት መር የሆነ ወታደራዊ ኃይል መገንባት ተችሏል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አሁን የደረሰበት የወታደራዊና የቴክኖሎጂ አቅም፣ ሀገርን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት የመከላከል ብቃቱን ከማረጋገጡ ባሻገር የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ የኃይል ሚዛን ሆኖ ወጥቷል።
ይህ በየጊዜው እያደገ የሚሄደው የልዩ ስልጠና፣ የዘመናዊ ትጥቅና የጠንካራ አስተዳደር ቅንጅት ሠራዊቱ የታሪካዊ ድል አድራጊነቱን ዘውድ እንደደፋ ወደፊት እንዲገሰግስና የኢትዮጵያን ዘላቂ ሕልውና እና ሁንተናዊ ብልጽግና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያስቀጥል ያስችለዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: