በደርግ ውድቀት ማግስት “አጥፍቶ መጥፋት” በሚል ርዕስ በዮሐንስ ሙሉጌታ (የጋዜጠኛና ደራሲ ሙሉጌታ ሉሌ የብዕር ስም) የታተመውን መጽሐፍ ያነበበ ሰው፣ የደርግ ሥርዓት የነበረበት የሥልጣን አያያዝ ችግርና ግትርነት እንዴት ለራሱ ውድቀት ምክንያት እንደሆነው በግልጽ ይረዳል።
ደራሲው በወቅቱ በፕሮፓጋንዳ ይቀርብ የነበረውን ገጽታ ወደ ጎን በመተው፣ የሥርዓቱን ውስጣዊ ድክመትና የአመራሩን ክፍተት በጥሩ ትረካ አሳይቶናል።
ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላም፣ ህወሓት በተመሳሳይ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ማለፉን መታዘብ ይቻላል። ሀገርን ለ27 ዓመታት በበላይነት የመራና ራሱን “አውራ ፓርቲ” አድርጎ ይገልጽ የነበረ ድርጅት፣ የጊዜውን ለውጥ ባለመረዳትና በውስጣዊ የፖለቲካ ስሌት ስህተት ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነበረበት የሥልጣን ማማ መውረዱ፣ የደራሲውን “አጥፍቶ መጥፋት” የሚለውን የታሪክ ርዕስ ዳግም የሚያስታውስ ክስተት ሆኗል።
የድርጅቱ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ባህል የውይይትና የድርድር አማራጮችን ከማስቀደም ይልቅ፣ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ነበር። ይህ አካሄድ ደግሞ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከሰቱት ፖለቲካዊ ክስተቶችም የዚህ የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት ማሳያዎች ናቸው።
በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ፣ ህወሓት የሰላም፣ የዕርቅና የለውጡ አካል እንዲሆን በርካታ ሀገራዊ ጥሪዎች ቀርበውለት ነበር።
ሀገርን የመራትና በዓለም አቀፍ መድረኮችም የተወከለበትን የፖለቲካ ምህዳር በሰላማዊ መንገድ እንዲቀላቀል የተዘረጉለትን የእርቅ እጆች በሙሉ በእብሪትና በንቀት ገፍቷል።
የለውጡን ሂደት ለመቀበል ከመዘጋጀት ይልቅ በትግራይ ክልል አጥር አጥሮ በመቀመጥ ኢትዮጵያን ለማወክ፣ ግጭቶችን ለማነሳሳት እና ሀገራዊ ተቋማትን ለማዳከም ቀን ከሌሊት ሠርቷል።
የድርጅቱ ቆሞ ቀርነት እና ስሌት አልቦነት ጎልቶ የወጣው በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ያልተጠበቀ ጥቃት ነው።
አብረውት የኖሩትን የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ሲጠብቁ የነበሩትን የመከላከያ አባላት “መብረቃዊ ጥቃት” በሚል ሰበብ ከጀርባ በመውጋት በታሪክ ያልታየ የክህደት ድርጊት ፈጽሟል።
ይህ ውሳኔ ድርጅቱ የታጠቀውን ጦር ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የትግራይን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለአደጋ የዳረገ አጥፍቶ የመጥፋት ስሌት ነበር።
ህገወጡ ህወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ የሰላም ቋንቋ የማይገባው፣ የትግራይን ወጣት ለጦርነት ማገዶ በማድረግና በሞታቸው የሚያተርፍ ድርጅት መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።
በመጀመሪያው ጦርነት የታየውን እጅግ አሰቃቂ የሰው ሕይወት መጥፋት ሳይማርበት፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር ጦርነቶች አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችንና ታዳጊዎችን ወደ ጦርነት ማግዷል።
የሰላም አማራጮችን እና የፌደራል መንግሥቱን የሰብዓዊ ተኩስ ማቆም ውሳኔዎች እንደ ድክመት በመቁጠር በእብሪት ተወጥሮ እስከ አፋርና አማራ ክልሎች ዘልቆ በመግባት ከፍተኛ የንብረት ውድመት፣ የዜጎች ግድያ እና አስነዋሪ ድርጊቶችን ፈጽሟል።
ይህም ድርጅቱ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ዓይነት ደንታ እንደሌለውና ብቸኛ ዓላማው ወደ ሥልጣን መመለስ ወይም አጥፍቶ መጥፋት እንደነበር ያረጋገጠ ነው።
የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ “አጥፍቶ መጥፋት” መጽሐፍ የደርግን ውድቀት እንዳሰየን ሁሉ፣ የህወሓት መጨረሻም በገዛ እጁ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ መጠናቀቅ ሆኗል።
የፖለቲካ ንቀት፣ የበላይነት አስተሳሰብ እና የትግራይን ሕዝብ ለራሱ የሥልጣን ማቆያ መጠቀሚያ የማድረግ አደገኛ አካሄድ ድርጅቱን ወደ ታሪክ ማህደር አሰናብቶታል።
በሕዝብና በሀገር ላይ የተፈጸመው ይህ የጥፋት ስሌት አካሄድ እንዳይደገም ለትውልድ የታሪክ መማሪያ ሆኖ ይኖራል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: