Search

የአዲስ አበባን ገጽታ እና ኢኮኖሚን የለወጠው የኮሪደር ልማት

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 53

በመደመር ዕሳቤ የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት ሥራዎች የነበሩ መልካም አጋጣሚዎችን በማስፋት እና ክፍተቶችን በማረም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዐበይት ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በከተሞች እና በገጠሩ የሀገራችን ክፍሎች እየተከናወኑ ያሉት ግዙፍ የመሠረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ሥራዎች የዚሁ ዘመን ተሻጋሪ ጥረት ዋና ማሳያ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፣ "የእኛ ርዕይ ለዛሬውና ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ ብቻ ሳትሆን ምርታማና ሁሉንም አካታች እንዲሁም ሕዝቧን የምትመጥን ከተማ መገንባት ነው ብለዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት እንደሚያመላክተው፣ የኮሪደር ልማቱ ዋና ግብ የከተማ ውበትን ከመፍጠር አልፎ የዜጎችን ሁለንተናዊ የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል እና የምርታማነት አቅምን የሚያሳድግ መሠረት መሆኑን ነው።

በዚሁ መሠረት በቅርቡ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ቀደም ሲል ችላ ተብለው የነበሩ የከተማዋን የወንዝ ተፋሰሶች ወደ አረንጓዴ የልማት እና የቱሪዝም ማዕከልነት የለወጠ ታሪካዊ እርምጃ ሆኗል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ማለትም ከፒያሳ እስከ መስቀል አደባባይ፣ ከቦሌ እስከ አራት ኪሎ እንዲሁም በካዛንችስ እና በለገሃር መስመሮች የተካሄዱት የተቀናጁ የኮሪደር ልማቶች የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት እና የእግረኛ መንገዶች ምቹና ደኅንነታቸው የተጠበቀ አድርጓቸዋል።

ይህም አዲስ አበባን ለአፍሪካ እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተመራጭ መዲና ከማድረግ በላይ የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት እንግልት በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል።

የዚህ ልዩ የኮሪደር ልማት ሌላው ዐበይት ፋይዳ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ዕውን ማድረጉ ነው። በአካባቢው የተገነቡት የተለያዩ የንግድ ማዕከላት ለሺዎች የሥራ እና የገቢ ምንጭ በመሆን የአምራቹን፣ የነጋዴውን እና የሸማቹን ትሥሥር በማጠናከር የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በአዲስ መልክ እያነቃቃ ይገኛል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የዛሬውን ትውልድ ፍላጎት ከመመለስ ባሻገር ለነገው ትውልድ ሙሉ የሆነች እና የበለጸገች ሀገርን ለማስረከብ የሚከወኑ ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ ሀብቶች ናቸው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: