በአየር ላይ በሚደረግ ረጅም እና አድካሚ ጉዞ መሃል የሚፈጠር አንዲት ትንሽ የርህራሄና የደግነት ተግባር የሰዎችን ህይወት እስከ ማሳየት ድረስ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
ታዋቂዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ሮቢን ሊ ክሪል ከቤተሰቧ ጋር በምታደርገው ጉዞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተናጋጅ የተደረገላትን የሰብአዊነት ድጋፍ በኤክስ ገጿ ላይ በማጋራት ልብ የሚነካ ምስጋና አቅርባለች።
ጋዜጠኛዋ ከባህሬን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ፣ ከዚያም ወደ መኖሪያ ቤቷ ቡላዋዮ ዚምባብዌ ረጅም ጉዞ በምታደርግበት ወቅት መላው ቤተሰቧ በእንቅልፍ ተሸንፈው ነበር።
ነገር ግን ስትነቃ የ4 ዓመት ህፃን ልጇ ከምትቀመጥበት ወንበር ላይ አልነበረችም። በድንጋጤ ጥቂት ረድፎች ከፍ ብላ ስትፈልግም ልጇ ሊዲያ በተባለች የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተናጋጅ እቅፍ ውስጥ ሰላም አግኝታ ተኝታ አገኘቻት።
ትንሿ ልጅ ነቅታ አልቅሳና ግራ ተጋብታ በነበረበት ሰዓት አስተናጋጇ ሊዲያ እናቷን ማስቸገር ስላልፈለገች ልጇን በራሷ እቅፍ አፅናንታ ታስተኛታለች።
ህፃኗም ቀሪዎቹን ሦስት ሰዓታት በአስተናጋጇ እቅፍ ውስጥ ሰላማዊ እንቅልፍ በመተኛት አሳልፋለች። ጋዜጠኛ ሮቢን ሊ ክሪል ይህንን ድንቅ የደግነት ተግባር ስትገልጽ፤ "በዚያ ሁሉ አድካሚ ጉዞ መካከል የተደረገልን ይህ ድንቅ የደግነት ተግባር ለእኛ ትልቅ ትርጉም ነበረው፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድን እና በተለይም ሊዲያን ከልብ እናመሰግናለን" ብላለች።
ይህ አስደናቂ ታሪክ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተሳፋሪዎቹ ከሚሰጠው ሙያዊ አገልግሎት ባሻገር፣ ኢትዮጵያውያን የባለቤትነትና የሰብአዊነት ስሜት በዓለም አቀፍ ደረጃ በድጋሚ ያስመሰከሩበት ድንቅ ክስተት ሆኗል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: