Search

የባሎን ዶር ሽልማት ከትንሿ አዳራሽ እስከ ዓለም አቀፉ ታላቅ መድረክ ያደረገው አስደናቂ ጉዞ እና የዛሬው ምሽት ደማቅ ትዕይንት

ሰኞ ጥቅምት 16, 2019 87

በፈረንሳዩ ጋዜጣ ‘ፍራንስ ፉትቦል’ አዘጋጆች በአውሮፓውያኑ 1956 የተጀመረውና በመጀመሪያው ዙር ሰር ስታንሊ ማቲውስ በብላክፑል አነስተኛ አዳራሽ ውስጥ የተሸለመው የባሎን ዶር ክብር ሰባት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ በለንደኑ ‘ፓላዲየም’ አዳራሽ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እግር ኳስ አፍቃሪያን በቀጥታ በሚከታተሉት ደማቅ የቀይ ምንጣፍ ስነ-ስርዓት የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ትዕይንት ሆኗል።

መጀመሪያ ላይ ጋዜጣው ሽያጩን ለማሳደግ በሚል ለአውሮፓውያን ተጫዋቾች ብቻ ወስኖ የጀመረው በመሆኑ እንደ ፔሌ እና ዲዬጎ ማራዶና ያሉ የእግር ኳሱ ዓለም ፈርጦች በታሪክ መዝገቡ ላይ ሳይካተቱ አልፈዋል።

ውድድሩ ከአውሮፓውያኑ 1995 ጀምሮ በአውሮፓ ውስጥ ለሚጫወቱ የሁሉም ሀገራት ተጫዋቾች፣ ከ2007 በኋላ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ተደርጓል።

ሽልማቱ በወቅቱ በነበረው ዝቅተኛ ዕውቅና ምክንያት በአውሮፓውያኑ 2001 አሸናፊ የነበረው ማይክል ኦውን “ስለ ሽልማቱ ሰምቼ አላውቅም ነበር” እስከማለት ቢደርስም፣ ዛሬ ግን የእግር ኳሱ ዓለም ዋነኛ የትኩረት ማዕከል ለመሆን በቅቷል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ እውቅናው እያደገ ቢመጣም፣ ለውድድሩ ተወዳጅነት ማደግ እና ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ መሆን ዋነኛውን ድርሻ የተጫወተው ግን የሊዮኔል ሜሲ እና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት አስርት ዓመታትን የተጠጋ ብርቱ ፉክክር ነው።

በአሁኑ ወቅት የባሎን ዶር መድረክ ከስፖርታዊ ክብር ባለፈ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበትና የተጫዋቾችን የገበያ ዋጋ የሚወስን ግዙፍ ተቋም ሆኗል።

ክብሩ እጅግ ከመግነኑ የተነሳ እንደ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ያሉ ኮከቦች ሽልማቱን ማሸነፍ ከሻምፒዮንስ ሊግ ወይም ከፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ በላይ እንደሚበልጥባቸው እስከመናገር ደርሰዋል።

አልፎ ተርፎም በ2024 ሮድሪ ቪኒሲየስ ጁኒየርን በልጦ በማሸነፉ ሪያል ማድሪድ በዝግጅቱ ላይ ላለመታደም የደረሰበት ውሳኔ ክብሩ በክለቦች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ያሳየ ሆኖ አልፏል።

ይህ አይነቱ አካሄድ ተጫዋቾች ከቡድን ስኬት ይልቅ ለግል ክብር ቅድሚያ እንዲሰጡ እያደረገ ነው በሚል እንደ አንጋፋዎቹ አርሰን ቬንገር እና ጆዜ ሞሪንሆ ባሉ የእግር ኳስ ጠበብት ዘንድ “ራስ ወዳድነትን ያበረታታል” የሚል ትችት ቢሰነዘርበትም የክብሩ ተፈላጊነት ግን ይበልጥ እየጨመረ መጥቷል።

በተለይም ከ2018 ጀምሮ የሴቶች ዘርፍ ሽልማትም መካተቱ ለዝግጅቱ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል።

በቲዬሪ ሄንሪ እና ኬት ስኮት በሚመራውና ከሁለት ሺህ በላይ ታዳሚዎች በሚገኙበት በዛሬው ታላቅ ምሽት በወንዶችና በሴቶች ዘርፍ በአጠቃላይ ለዕጩነት የቀረቡት 60 ተጫዋቾችና 10 አሰልጣኞች በለንደኑ ስነ-ስርዓት እንደሚታደሙ ይጠበቃል።

ታዲያ የዛሬውን ደማቅ ምሽት የወንዶችና የሴቶች የባሎን ዶር ክብር ማን የሚያነሳ ይመስላችኋል? ግምትና አስተያየታችሁን  በኮመንት ላይ አስፍሩልን።

 

በዘረንቶስ ሰለሞን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: