ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜ እና ቦታ በሀገራቸው አንድነት ላይ የመጡ ወራሪዎችን በጋራ የመከቱ ሲሆን፤ አያሌ የደም መስዕዋትነት በመክፈልም ሀገራቸውን ጠብቀዋል፡፡
ነገር ግን በግዛት አንድነታቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ከሚከፍሉት የደም መስዕዋትነት ባሻገር በሚፈለገው መጠን በላብ መስዕዋትነት ላይ አንድነታቸውን ባለማሳየታቸው እድገታቸው የተገደበ ሆኖ መቆየቱን ዶ/ር ደረጄ እንግዳ ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር ደረጄ እንግዳ ከኢቲቪ ዜና 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የላብ መስዕዋትነት የሚያስገኛቸው ድሎች ምን ያህል ጣፋጭ እንደሆኑ ለማየት የሕዳሴ ግድብን ማየት ብቻ በቂ ነው ብለዋል፡፡
ከውጭ የመጣን ወራሪ በጋራ እንደምንመክተው ሁሉ ከድህነት ለመውጣት በጋራ የመስራት እና በጋራ ሆኖ ከድህነት ለመላቀቅ ሀገራዊ አንድነት የግድ መሆኑን አንስተዋል።
እኛ ትናንት ስንረዳቸው የነበሩ ደቡብ ኮሪያውያን እንኳን የነበረባቸውን ጦርነት አጠናቀው ፊታቸውን ወደ ልማት በማዞራቸው እና ህዝቦቻቸው በከፈሉት የላብ መስዕዋትነት ዛሬ በዓለም ላይ ግዙፍ የተባለለትን ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን አላስፈላጊ በሆኑ ከፋፋይ ትርክቶች ያጠፋነው ጊዜ ሊቆጨን ይገባል ያሉት ዶ/ር ደረጄ፤ የላብ መስዕዋትነት የሚያስገኛቸው ድሎች ምን ያህል ጣፋጭ እንደሆኑ ለማየት የሕዳሴ ግድብን ማየት ብቻ በቂ ነው ሲሉ አንስተዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ በስራ ላይ ትገኛለች ያሉት ዶ/ር ደረጄ፤ በላብ መስዕዋትነት ሀገሩን ለማበልጸግ የተነሳ አመራር እና ትውልድ ተፈጥሯል ብለዋል።
አሁን በኢትዮጵያ በሚሰሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ ጠንካራ የስራ ባህል አስተሳሰብ እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
24 ሰዓት ያለማቋረጥ የሚሰራ ሀገሩን ይበልጥ በልፅጋ ማየት የሚፈልግ ትውልድ በዚህ አመራር ተፈጥሯል ሲሉም አክለዋል፡፡
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD